Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ተማሪዎችን አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን  6 ሺህ 244 ተማሪዎችን አስመረቀ፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይን ጨምሮ ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዓላማ የሰለጠነና ብቃት ያለው የሰው ኃይል እንዲሁም ለስራ ፈጠራ የተዘጋጀ የሰው ኃይል እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡

ተመራቂዎች በሰለጠናችሁበት ሙያ ያገኛችሁትን ሙያዊ እውቀት፣ ክህሎትና ስነ-ምግባር በመጠቀም ስራ በመፍጠር ጥራት ያለውና ተፈላጊ በመሆን እንዲሁም ተወዳዳሪ የሆነ የምርት አገልግሎትን በማቅረብ ሂደታችሁን ውጤታማ እንደምታደርጉ እምነት አለን ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ተመራቂዎች በሰለጠኑበት የሙያ መስክ በመሰማራት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማሸጋገር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

አክለውም ፥ ኢንዱስትሪውን በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በማድረግ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚም እንደሚያሳድጉ ተስፋ ተጥሎባችኋል ሲሉም ነው የጠቆሙት፡፡

ተመራቂዎች የቀሰሙትን ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ከራሳችሁ አልፈው ለሌሎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ፣ ተወዳዳሪና ጥራት ያለው ምርት በማምረት ሀገር የሚያኮሩ እንዲሁም ትጉህ ዜጋ ለመሆንም በርትተው እንዲሰሩም ከንቲባዋ አደራ ሰጥተዋል፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷል፡፡

 

 

Exit mobile version