Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ሰብረው የገቡ 5 ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 5 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ሰብረው የገቡ 5 ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ ተቀጥተዋል፡፡

ቅጣቱን የወሰነው የሸገር ከተማ አስተዳደር የኮዬ ፌጬ ክ/ከ ወረዳ ፍርድ ቤት ነው።

የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሾች፥ ነኢማ አብዲልጀሊል፣ ባሩዲን አሉ፣ ደሲቱ አብዱጀሊል፣ ኑረዲን መሀመድ እና ሪያድ ጀማል ናቸው።

የሸገር ከተማ የኮዬ ፌጬ ክ/ከ ዐቃቤ ህግ ግለሰቦቹ ሐምሌ 2015 ዓ.ም የኮዬፌጬ የመንግስት ኮንዶሚኒየም ቤት በተደረገ ቆጠራ ህገ ወጥ ድርጊቱን መፈጸማቸውን ተከትሎ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በመጥቀስ ክስ መስርቶባቸዋል።

በክሱም የቤቶች ልማት አስተዳደርና ማስተላለፍ አዋጅ ቁጥር 231/2013 አንቀጽ 69 ንዑስ ቁጥር 1 እና አንቀጽ 86 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ግለሰቦቹ ተላልፈዋል የሚል ክስ ዝርዝር ቀርቧል።

ተከሳሾቹ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበው በደላላ አማካኝነት መግባታቸውን ጠቅሰው ቃላቸውን ሰጥተዋል።

መዝገቡን የመረመረው የወረዳ ፍ/ቤቱ የመንግስት ቤትን ሰብረው መግባታቸው በማስረጃ ማረጋገጡን ገልጾ በእያንዳንዳቸው ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

ፍርድ ቤቱም በግለሰቦቹ የተፈጸመው ድርጊት ህገወጥ ተግባር መሆኑን በማብራራት ከአምስቱ ግለሰቦች መካከል አራቱን በ4 ወራት ቀላል እስራት እና ከ500 ብር እስከ 2ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ አስተላልፎባቸዋል።

ሌላኛው ባሩዲን አሊ የተባለ ግለሰብን በሚመለከት ደግሞ በ3 ወራት ቀላል እስራትና 500 ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ተወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version