አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ከሚገኙት የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ÷ በኢትዮጵያና በተቋሙ መካከል ባሉ የጋራ ጉዳዮች ና መልካም ግንኙነታቸው ይበልጥ መጠናከር በሚችልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
በተጨማሪም ÷ ኢትዮጵያ ቅድሚያ በምትሰጣቸው የልማት መስኮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
አቶ አህመድ ሺዴ በአለም ባንክ የሚደገፉ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ ለዋንኞቹ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አንስተዋል፡፡
በኢትዮጵያና በአለም ባንክ መካከል ያለው የልማት ትብብር ዘላቂና አካታች እድገት ለማስመዝብ እንደሚያግዝ ም አመላክተዋል፡፡
በተሻሻለ ምርታማነትና በተወዳዳሪነት መንፈስ ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን ለማፋጠን የታቀደውን ሁለተኛውን የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ሊያጋጥሙ ስለሚችሉት መልካም እድሎችና ፈተናዎችም ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
ከሀገሪቱ የልማት ፍላጎትና ከማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች አንጻር ሀገሪቱ ይህን ግዙፍ ማሻሻያ አጀንዳ ውጤታማ በሆነ መልኩ ተግባራዊ እንድታደርግ የአለም ባንክ ድጋፉን እንዲሰጥ የባንኩን ፕሬዚዳንት ጠይቀዋል፡፡
ድህነት እያስከተለ ያለውን ልዩ ተግዳሮት ታሳቢ ያደረገ ምላሽ ከባንኩ የማሻሻያ ሂደት እንደሚጠብቁና በተለይም የባንኩ ድጋፍ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት አንገብጋቢ ፍላጎት ጋር መጣጣሙን በተመለከተ ለውጥ እንሚጠብቁም አቶ አህመድ ሽዴ ተናግረዋል፡፡
ባንኩ ባካሄደው የለውጥ ሂደት በአጭር ጊዜ ውስጥ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እንዲሁም የባንኩን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ በቅርቡ የተወሰዱትን ውጤታማ እርምጃዎች አስመልክቶም ለፕሬዚዳንቱ ምስጋና ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡