አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና ቤጂንግ ከፈረንጆቹ ሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 2 ቀን 2023 በ140 ዓመታት ታሪክ ውስጥ አጋጥሞ የማያውቅ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ መጣሉ ተገለጸ።
ከተማዋ በቅዳሜ እና ረቡዕ ጠዋት መካከል 744 ነጥብ 8 ሚሊ ሜትር ዝናብ መመዝገቡን የቤጂንግ ሚቲዎሮሎጂ ቢሮ አስታውቋል።
ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊመዘገብ የቻለው÷ ደቡባዊ ቻይና ግዛቶችን የመታው ታይፎን ዶክሱሪ የተሰኘው ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ነፋስ ወደ ሰሜናዊ ቻይና ግዛቶች በመዞሩ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
በቤጂንግ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደጣለ የተመዘገበው ከፈረንጆቹ ሐምሌ 23 እስከ 29 ቀን 1883 ባሉት ቀናት 510 ነጥብ 3 ሚሊ ሜትር እንዲሁም ሐምሌ 23 ቀን 1891 ደግሞ 609 ሚሊ ሜትር እንደነበር ሲጂ ቲ ኤን ዘግቧል።