አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤች አይ ቪ/ኤድስ ሥርጭት በወጣቶች አዲስ የመያዝ እና ከእናት ወደልጅ የመተላለፍ ምጣኔ በሚፈለገው ልክ ዝቅ አለማለቱን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በመሆኑም እነዚህን የሕብረተሰብ ክፍሎች መሰረት ያደረገ ሥራ እንደሚጠበቅ በሚኒስቴሩ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽሕፈት ቤት ገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ/ኤድስ እንዳለባቸው ከሚገመቱት 610 ሺህ 350 ወገኖች መካከል 61 በመቶ ሴቶች እና 39 በመቶ ወንዶች መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ በየዓመቱ 8 ሺህ 257 ሰዎች በኤች አይ ቪ/ኤድስ የሚያዙ ሲሆን 11 ሺህ 322 ወገኖች ደግሞ በበሽታው ምክንያት ሕይወታቸው ያልፋል፡፡
እንደሀገር የኤች አይ ቪ/ኤድስ የሥርጭት መጠን 0 ነጥብ 91 በመቶ መሆኑ ተስፋ ሰጭ ቢሆንም÷ በጋምቤላ ክልል 3 ነጥብ 7፣ በአዲስ አበባ ከተማ 3 ነጥብ 1፣ በድሬዳዋ ከተማ 2 ነጥብ 69 እና በሐረሪ ክልል 2 ነጥብ 55 በመቶ መሆኑ አሳሳቢ ሆኗል ተብሏል፡፡
በሚኒስቴሩ የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽ/ቤት መሪ ስራ አስፈጻሚ ፈቃዱ ያደታ÷ የምርመራ ኪቶችና መሰል ቁሶች የሚገዙት ለነፍሰጡሮች፣ በይበልጥ ተጋላጭና ትኩረት ለሚሹ ወገኖች ነው ብለዋል፡፡
ሴተኛ አዳሪዎች፣ አፍላ ወጣቶችና ወጣት ሴቶች፣ ረዥም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ የሕግ ታራሚዎች እና ለሱስ ተጋላጮች÷ በይበልጥ ለቫይረሱ ተጋላጭና ትኩረት የሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ከቫይረሱ ሥርጭት እና ተያያዥ ጉዳዮች አንጻር ከ1 ሺህ በላይ ወረዳዎች÷ ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ሥርጭት ያለባቸው ተብለው መለየታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
በይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑት÷ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት፣ የአቻ ለአቻ ውይይት፣ የምርመራ ሥራ፣ ከትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ፖዘቲቭ ቢሆኑ ለሌላኛው የመከላከያ መድኃኒት የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!