Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአይሲቲ ልማትና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ በጋራ ለመስራትና ትብብሮችን ለማጠናከር ያለመ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከቻይና የአይሲቲ ሶሉሽንስ አቅራቢ ድርጅት “ዜድ ቲ ኢ” ኮርፖሬሽን ጋር በአይሲቲ ልማትና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እና በዜድቲኢ ኮርፖሬሽን ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት ምክትል ፕሬዚዳንት ዬ ዢያኦሃን ፈርመውታል።

ስምምነቱ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የአይ ሲቲ ልማት በማስፋፋትና የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በማስፈጸም ትብብሮችን ለማጠናከር እንዲሁም ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ ያለመ ነው ተብሏል።

በዚሁ መሰረት ኮርፖሬሽኑ በሚኒስቴሩ የታቀዱትን የዲጂታል መሠረተ ልማት ዝርጋታ ቴክኒካዊ ድጋፍ ለመስጠት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማረጋገጥ እንዲሁም የስራ እና ሃብት ፈጠራ ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የአይሲቲ ፕሮጀክቶች፣ የኦንላይን ኢ- ለርኒንግ ፕላትፎርሞች እና በኢትዮጵያ የተርሚናል የማምረቻ ፋብሪካ የመመስረት እቅድን ያካተተ ነውም ተብሏል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ የአይሲቲ ፓርክ ግንባታ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በመደገፍና በመሳተፍ ለፓርኩ ተልዕኮ ስኬት የበኩሉን እንደሚያበረክት ተጠቁሟል።

ዜድቲኢ በኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2005 ጀምሮ በቴሌኮም መሰረተ ልማት ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ ነውም ተብሏል፡፡

 

Exit mobile version