አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ወቅታዊ የግንባታ ቁሳቁስ እጥረት እና የመድረክ ዲዛይን ሥራ አለመጠናቀቅ የብሔራዊ ቴአትር ቤት ግንባታን እያጓተተው መሆኑ ተጠቆመ፡፡
በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የፌደራል መንግስት ሕንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ዛህራ አብዱልሃዲ (ኢ/ር)፥ ባለፈው ዓመት የተጀመረውን የብሔራዊ ቴአትር ቤት ግንባታ የካቲት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ውል መገባቱን አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ የግንባታው ሂደት አሁን ላይ 12 ነጥብ 8 በመቶ መድረስ ሲገባው÷ 8 ነጥብ 6 በመቶ ላይ መሆኑን ነው የገለጹት።
ግንባታው በተጀመረ ሰሞን በፍጥነት እየሄደ እንደነበር አስታውሰው፥ በአሁኑ ወቅት ግን በታሰበው ልክ እየሄደ አይደለም ብለዋል፡፡
የግንባታ ቁሳቁስ እጥረት እና የዋጋ ግሽበት እንዲሁም ከመድረክ ስራው ጋር ተያይዞ የዋጋ ብሎም የዲዛይን ችግር ባለመፈታቱ ምክንያት የግንባታ ሂደቱ መጓተቱን አመልክተዋል።
በ7 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ለሚያርፈው የቴአትር ቤቱ ግንባታ 2 ቢሊየን 727 ሚሊየን 666 ሺህ 141 ብር መመደቡን ገልጸዋል፡፡
ወጪውም በፌዴራል መንግስት ሕንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ይሸፈናል ሲሉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ሕንጻውም ባለ 11 ወለል መሆኑን ጠቅሰው የዘመናዊ መድረክን ጨምሮ ተያያዥ ግንባታዎች እንዲኖሩት ተደርጎ እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!