Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በማጭበርበር ድርጊት ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ግለሰቦች ተከሰሱ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “ከሶማሌ ክልል የተፈናቀልን ነን” በማለት በማጭበርበር በመንግሥት ላይ ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ 50 ግለሰቦች ተከሰሱ።

ክሱ የቀረበው በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት ነው።

ተከሳሾቹም÷ ብርሃኑ ግርማ፣ ደረጄ ጌታቸው፣ ዱቦእ ፉፋ እና ሙሳ አብዲን ጨምሮ 50 ናቸው።

የኦሮሚያ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ሦስት ክሶችን አቅርቧል።

በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና አንቀጽ 696 (ሐ) ስር የተመለከተውን እንዲሁም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 4 ንዑስ ቁጥር 4፣ አንቀጽ 23 (2.3) እና አንቀጽ 32 (3.2) ላይ የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል ተብለው ክሱ በዝርዝር ቀርቦባቸዋል፡፡

በተለይም በመጀመሪያው ክስ ከ1ኛ እስከ 5 ኛ የተጠቀሱ ተከሳሾች ከሶማሌ ክልል በግጭት ምክንያት ከአዋሳኝ የኦሮሚያ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ 1 ሺህ 854 ዜጎች ኮሚቴ ሆነው ሲሰሩ ከአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በተጻፈ የዕርዳታና ድጎማ ደብዳቤ መነሻ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በወቅቱ በኮዬ ፌጬ አካባቢ ለተፈናቃዮች ቤት እንዲሰራ በወሰነው ውሳኔ መሰረት ለተፈናቃዮች የድጋፍና ድጎማ ስራ ሲጀምር ጥር 16 ቀን 2010 ዓ.ም ተፈናቃይ ያልሆኑ ግለሰቦች በሀሰተኛ ጊዜያዊ መታወቂያና ሰነድ ዝርዝር እንዲካተት አድርገዋል ተብሎ በክሱ ተጠቅሷል።

በዚህ ተፈናቃይ ዜጎችን የመደጎምና የመኖሪያ ቤት የመስጠት ሂደት ውስጥ ከ5ኛ እስከ 30ኛ የተጠቀሱ ተከሳሾች ተፈናቃይ ነን በማለት ሀሰተኛ የተፈናቃይ ጊዜያዊ መታወቂያና የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን በማቅረብ በማጭበርበር በእርዳታ ድጎማው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉም ተብራርቷል፡፡

በሌላኛው ክስ ደግሞ ከ31ኛ እስከ 50ኛ በክሱ የተጠቀሱ ተከሳሾች በተለያየ ጊዜ ሀሰተኛ የተፈናቃይ መታወቂያዎችን እና ከሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ካምፓስ የተሰጡ የሚመስሉ ሀሰተኛ ሰነዶችን በተለያየ ስም በማቅረብ ተሳትፎ ያላቸው ተከሳሾች መኖራቸው ተገልጿል፡፡

50 ዎቹ ተከሳሾች በጥቅም በመመሳጠር ተፈናቃይ ሳይሆኑ ተፈናቃይ እንደሆኑ የሚገልጹ ቅጾችን በመሙላትና በማስሞላት ጭምር ባደረጉት ተሳትፎ÷ በኮዬ ፈጬ አካባቢ እያንዳንዳቸው 705 ሺህ 225 ብር ከ04 ሳንቲም የሚገመት መኖሪያ ቤት ወስደዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

በተጨማሪም እያንዳንዳቸው በተለያየ ጊዜ 19 ሺህ 600 ብር ድጎማ በመቀበል በተፈጸመ የማጭበርበር የሙስና ወንጀል ድርጊት በመንግስት ላይ 8 ሚሊየን 697 ሺህ 876 ብር ከ08 ሳንቲም ጉዳት አድርሰዋል በሚል ዐቃቤ ሕግ የተከሳሾቹን ሚና ጠቅሶ ክስ መስርቷል፡፡

የወንጀሉን መፈፀም ያስረዳሉ ያላቸውን የተቋማት፣ የሰነድ ማስረጃዎችን እና የሰው ምስክር አቅርቧል።

የኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎትም ክሱን ለመመልከት ለነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version