አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 29፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የምርጫውን መራዘም እንደሚደግፉ በጋምቤላ ክልል የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ።
ብልጽግናን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ አራት ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫና በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ትናንት በጋምቤላ ከተማ ተወያይተዋል።
በዚሁ ጊዜ የፓርቲዎቹ አመራሮች እንዳሉት ምርጫ ቦርድ በኮሮና ወርርሽኝ ምክንያት ምርጫ ለማካሄድ የገጠመውን ችግር መነሻ በማድረግ የምርጫውን መራዘም እንደሚደግፉት ገልፀዋል ።
ከፓርቲ አመራሮች መካከል የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅነቄ/ጋህነን/ ሊቀመንበር አቶ ፒተር አማን እንደተናገሩት፥ በሀገሪቱ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ምርጫው እንዲራዘም የቀረበው አማራጭ የሚደገፍ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ተባብሮ ህዝብና ሀገርን ማዳን ነው ያሉት አቶ ፒተር ጋህነን፥ ከገዥ ፓርቲና ከመንግስት ጋር በመሆን በሽታውን በመከላከሉ ስራ ላይ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ከምርጫ በፊት ህዝብንና ሀገርን የማዳን ስራ መቅደም አለበት ያሉት ደግሞ ሌላው የጋህነን አመራር አቶ ተዘራ ኃይለማሪያም ናቸው።
በመሆኑም ምርጫው እንዲራዘም የቀረበውን ሃሳብ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ገልፀዋል ።
በኢዜማ የጋምቤላ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኡቻን ኡጎቶ እንደሚሉት ደግም አሁን ላይ የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሁን መቅደም ያለበት ህዝቡን ከኮሮና ቫይረስ የመታደጉ ተግባር ነው ብለዋል።
በመሆኑም መንግስት ምርጫው እንዲራዘም የወሰደው አማራጭ ትክክለኛና ፓርቲያቸው የሚደግፈው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ምርጫው እንዲራዘም ማድረግ ተገቢ ቢሆንም ከስድስት ወራት በላይ ማለፍ የለበትም የሚል ሃሰብ ያነሱት ደግሞ የጋምቤላ ህዝቦች ፍትህ ሰላም ልማት ዴሞክራሲ ንቅናቄ /ጋህፍሰልዴን/ ሊቀመንበር አቶ ሳይመን ቱት ናቸው ።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት መንግስት ምርጫው እንዲራዘም ፈልጎ ሳይሆን የህዝብ ጤንነትና የሀገር ደህንነት ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ጉዳይ በመሆኑ ነው ብለዋል።
መንግስት የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ሊያስከትል የሚችለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ቀውስ ለመሻጋር የተቻለውን ጥረት ሁሉ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የተከሰተውን ችግር ለመሻገር በክልሉ የሚገኙ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው በሽታውን በመከላከሉ ተግባር በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ስራ አስፈፃሚው መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

