Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአንበጣ መንጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በቀጣዩ ሣምንት የአውሮፕላን ርጭት ይጀመራል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአንበጣ መንጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በቀጣዩ ሣምንት በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት እንደሚጀመር ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

እስካሁን አንበጣው እንደሀገር ከፍተኛ ጉዳት አለማድረሱን የገለፀው ሚኒስቴሩ፥ በቀጣይም ጉዳት እንዳይደርስ እየተሠራ ነው ብሏል።

በሚኒስቴሩ የእጽዋት ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ በላይነህ ንጉሴ የአንበጣ መንጋው ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ወደ ሀገር ውስጥ አለመግባቱን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ግብርና ሚኒስቴር ከክልሎቹ ጋር በመቀናጀት የአንበጣ መንጋ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ጉዳት እንዳያደርስ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሚኒስቴሩ ለክልሎች የአንበጣ መንጋ መከላከያ ኬሚካል፣ የኬሚካል መርጫ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም የባለሙያዎች ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው፥ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት።

ወቅቱ ለአንበጣ መራባት ምቹ መሆኑን እና ለሰውም ሆነ ለተሽከርካሪ በማይመች ተራራማ ቦታ ላይ እያረፈ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በቀጣይ ሣምንት የአውሮፕላን ርጭት ይጀመራል ነው ያሉት፡፡

በ62 ሺህ 107 ሔክታር ላይ የበረሃ አንበጣ አሰሳ ተካሂዶ፥ በማደግ ላይ ያለ የበረሃ አንበጣ በትግራይ፣ አፋርና አማራ ክልሎች 12 ሺህ 653 ሔክታር መውረሩን አብራርተዋል።

ከዚህ ውስጥ 470 ሔክታር በባሕላዊ መንገድ መከላከል መቻሉን ነው ያስረዱት።

ዘንድሮ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ካለፈው ዓመት አንጻር ሲታይ የከፋ እንዳልሆነ የጠቀሱት አቶ በላይ÷ ባለፈው ዓመት በስድስት ክልሎችና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተከስቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version