አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚንስትር የነበሩት ዶ/ር ከበደ ታደሰ በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ዶ/ር ከበደ ከጥቅምት 1993 እስከ ጥቅምት 1998 በጤና ሚኒስቴር አገልግለዋል፡፡
በተጨማሪ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የማበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት÷ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የአመራር ክፍተት በገጠመው ጊዜ ከሁለት ዓመታት በላይ በቅርበት አመራርና ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረትም ማህበረሰብ-አቀፍ የጤና አገልግሎት ስልት እንዲነደፍ ዶክተር ከበደ አመራር መስጠታቸው ይታወቃል፡፡
እንዲሁም የተፋጠነ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ ያደረጉ ስለመሆናቸው የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በሙከራ ትግበራ ከማስጀመር ጎን ለጎን ተቋማዊ እንዲሆን ሥርዓተ-ትምህርት እንዲቀረፅና ስልጠና በሰፊው እንዲጀመር ያደረጉ ናቸው ዶ/ር ከበደ፡፡
የዓለም ማህበረሰብ ባደረገው አጋርነት ነጻ የፀረ-ኤች አይ ቪ/ኤድስ ሕክምና በጥር 1997 ዓ.ም እንዲጀመር ያደረጉትም ዶ/ር ከበደ ናቸው፡፡
የዶ/ር ከበደ ታደሰ የቀብር ሥነ ሥርዓት በነገው ዕለት ከቀኑ 6 ሰዓት በመንበረ ፀባኦት ቅድሥት ስላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ተገልጿል፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በዶ/ር ከበደ ታደሰ ኅልፈት የተሰማውን ሐዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቹ እና ወዳጆቹ መጽናናትን ይመኛል፡፡