Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአየር ትንበያ መረጃዎች ትክክለኛነት ደረጃ እስከ 80 በመቶ መድረሱን ኢንስቲትዩቱ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የምሰጣቸው የአየር ሁኔታ ትንበያዎች ከ70 እስከ 80 በመቶ ትክክለኛ መሆናቸውን በጥናት አረጋግጫለሁ ሲል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ።

ኢንስቲትዩቱ፥ የአጭር፣ መካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ተብለው የተለዩ የአየር ትንበያ መረጃዎችን ለተጠቃሚዎች ይሰጣል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የረጅም ጊዜ ትንበያና የድርቅ ክትትል ዴስክ ኃላፊ ሙሉዓለም አበራ እንዳሉት÷ ለተጠቃሚዎች የሚሰጡት የተተነተኑ እና የተሰበሰቡ ጥሬ መረጃዎች ናቸው፡፡

ተተንትነው የሚሰጡ መረጃዎችም÷ የግብርና፣ የጤና እና የውሃ ሚቲዎሮሎጂ ትንበያዎችን ምክረ ሐሳብ በማዘጋጀት ከ10 ቀናት እስከ 4 ወራት ጊዜ ያለውን እንደሚያካትቱ ነው የጠቆሙት፡፡

የትንበያዎች ትክክለኛነትም ሣይንሳዊ ዘዴን በመጠቀም እንደሚረጋገጥ አስገንዝበው÷ ኢንስቲትዩቱ ለአቪዬሽን ሚቲዎሮሎጂ በአውሮፕላን በረራ ወቅት የሚያስፈልጉ መረጃዎችን ይሰጣል ብለዋል፡፡

ትንበያዎች ሲሰጡም፥ ዓለም አቀፋዊ፣ አኅጉራዊ፣ ከባቢ አየራዊ፣ የውሃና የየብስ ተፅዕኖዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ብለዋል።

መረጃን ለተጠቃሚው በመስጠት የሚደርስን ጉዳት ለመቀነስና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረግ ጥረትም ኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

ከግብርና፣ ጤና፣ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴሮች፣ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እንዲሁም የአየር ንብረትና አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር  ብሔራዊ የአየር ንብረት አገልግሎት ማዕቀፍ ተፈርሞ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግሥታዊ የሆኑና ያልሆኑ ተቋማት፣ የምርምር ማዕከላት፣ ባለሀብቶች፣ ኮንስትራክሽን ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች፣ በኢንሹራንስ ዘርፍ የሚሠሩ አካላት የትንበያ መረጃ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

Exit mobile version