አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተሰሩ ቅንጅታዊ ስራዎች በኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ ሀገር ልታጣ የነበረውን ከ84 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገለፀ፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር ፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና የፍትህ ሚኒስቴር ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን በመከላከልና በመቆጣጠር በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በቅንጅት የተሰሩ ስራዎችን በተመለከተ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
በውይይቱ ላይ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ÷ ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ በሀገር ላይ እያሳደረ የሚገኘውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ለመመከት ኮሚሽኑ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተሰሩት ቅንጅታዊ ስራዎችም በኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ ሀገር ልታጣ የነበረውን ከ84 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን እንደ ተቻለ ጠቁመዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን የኢንተለጀንስና ኮንትሮባንድ መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ ተገኔ ደረሰ ÷ በየብስ ከሚደረገው የኮንትሮባንድ ዝውውር በተጨማሪ በአየር መንገድ በኩል የሚከናወነው የኮንትሮባንድ ዝውውር ችግሩን የበለጠ አሳሳቢና ውስብስብ እንዲሆን እንዳደረገው ጠቁመዋል::
በዚህም በ2015 የበጀት ዓመት በኤርፖርት ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ብቻ ከ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ የገቢና የወጭ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን መግለፃቸውን ከጉምሩክ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡