Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተለያየ ተግባር እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተለያየ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ለረጅም ዓመታት ቀረጥ ሲጣልባቸው ከነበሩ የቅንጦት እቃዎች ዝርዝር ውስጥ የነበረው የንፅህና መጠበቂያ ቁስ የጤና ሚኒስቴር በወሰነው መሰረት በመድሃኒት ጤና አገልግሎት ዘርፍ እንዲካተት መደረጉም ተመላክቷል፡፡

ይሁንና የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ሲገባ በአንድ እሽግ ምርት ላይ እስከ ግማሽ ድረስ የዋጋ ቅናሽ ሊያሳይ እንደሚችል ተነግሮ የነበረ ቢሆንም በተጠቃሚዎች ዘንድ ግን አሁንም እጥረቱ እንዳለ ይነሳል፡፡

በሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ላይ ተጥሎ የነበረዉን የ 30 በመቶ ታክስ ጭማሪ ወደ 10 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን የገለጹት በጤና ሚኒስቴር የወሽና አካባቢ ጤና አስተባባሪ ወንዳየሁ ዉቤ፤ ዓለም አቀፍ ግሽበቱ ግን በታሰበው ልክ ዉጤት እንዳይመጣ ማድረጉን ተናግረዋል።

የትምህርት መጠነ ማቋረጥን ለመቀነስ በሚልም ትምህርት ቤቶች ላይ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ በነፃ እንዲሰጥ እየተደረገ ነዉ ያሉት ወንዳየሁ ዉቤ፥ እስካሁን ድረስም በተለያዩ ፕሮጀክቶች አንድ ሺህ ሰማንያ ትምርት ቤቶች ላይ ማሰራጨት እንደተቻለ አንስተዋል፡፡

እጥረቱን ለመቅረፍም በህንድ የሚገኝ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ቁስ አምራች ኩባንያ ከመንግስት በቀረበለት ጥያቄ መሰረት ማምረቻ ፋብሪካዉን በኢትዮጵያ ዉስጥ ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በ 2008/9 ዓ.ም ገደማ ጤና ሚኒስቴር በ8 ክልሎች አጠናሁ ባለዉ መሰረት የተለያዩ ግኝቶች እንደነበሩ ጠቁሟል፡፡

63 በመቶ ልጃገረዶች ከማንም ጋር ስለወር አበባ እንደማይነጋገሩ፣ 22 በመቶ የሚሆኑ እናቶችም ለልጆቻቸዉ እንደማይናገሩ፣ 69 በመቶ የሚደርሱት ይህን ተፈጥሯዊ ዑደት አሳፋሪ ብለዉ እንደሚያምኑ፣ 59 በመቶዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመለከቱ እንደሚደነግጡ፣ 30 በመቶዎቹም ህመም መስሏቸዉ እንደሚጨነቁ እና 35 በመቶዉ ብቻ ግን መረጃዉ እንዳላቸዉ የሚኒስቴሩ ጥናት ያሳያል፡፡

በሀይማኖት ወንድራድ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version