አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ለ44 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ቤት አስተላለፈ።
በዚህም 185 ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ነው የተገለጸው።
ክፍለ ከተማው ከዚህ ባለፈም ለሙስሊም የህብረተሰብ ክፍሎች ለተለያዩ የምግብ ፍጆታ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።
እስካሁንም ለ2 ሺህ 200 ሙስሊሞች ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ የትናየት ሙሉጌታ ተናግረዋል።
እንዲሁም 150 የሚሆኑ አመራሮች ደም የለገሱ ሲሆን፥ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ሀላፊ ኢንጂነር እንዳወቅ አብጤ የከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ላለው ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሀላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ላለው ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ህብረተሰቡ በአሁኑ ወቅት እየተነገሩ ባሉ የተሳሳቱ የፖለቲካ አጀንዳዎች ሳይሸበር ትኩረቱን ኮሮናን መከላከል ላይ ሊያደርግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በጥበበስላሴ ጀንበሩ

