አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሳፋሪኮም የአፍሪካ ትልቁ የሞባይል ገንዘብ ማስተላለፊያ ‘ኤም-ፔሳ’ አገልግሎትን ከሶስት ወራት በኋላ ዛሬ በይፋ አገልግሎት ላይ እንደሚያውል ገለጸ።
አገልግሎቱ ለሦስት ወራት በሙከራ የቆየ፣ ቴክኒካል ዝግጁነቱን ያጠናቀቀ፣ ከባንኮች ጋር ቁልፍ አጋርነትን ያረጋገጠ እና ወኪሎችንም መልምሎ ሥልጠና የሰጠ መሆኑ መረጋገጡ ተገልጿል፡፡
ሁሉም የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ደንበኞች ‘ኤም-ፔሳ’ የሚያቀርበውን አገልግሎት በሳፋሪኮም መስመራቸው በአንድሮይድ እና በ(አይ ኦ ኤስ) በመደወል መጠቀም እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
መተግበሪያው በአሁኑ ጊዜ በአምስት ቋንቋዎች ለአንድሮይድ ስልኮች ዝግጁ እንደሆነና ፕሌይ ስቶር ላይ እንደሚገኝ በመግለፅ በሚቀጥሉት ሳምንታት ደግሞ ለ (አይ ኦ ኤስ) ስልኮች እንደሚቀርብ ተመላክቷል፡፡
‘ኤም-ፔሳ’ ን በመጠቀም ደንበኞች በሀገር ውስጥ ገንዘብ መላክ እና ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ገንዘብ መቀበል፣ ለነጋዴዎች ክፍያ መፈፀም፣ የአየር ሰአት መግዛት፣ ወደ ባንክ ሂሳባቸው ማስተላለፍ እና ከባንክ ሂሳባቸው ወደ ‘ኤም-ፔሳ’ መላክ እንደሚችሉ የድርጅቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
‘ኤም-ፔሳ’ በሚሊየን ለሚቆጠሩ ሰዎች የፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ በአፍሪካ በጣም ስኬታማ እንደሆነ ይነገርለታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!