አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትምህርት ቢሮ የተማሪና መጽሐፍ ጥምርታን 1 ለ 1 ለማድረግ 1 ሚሊየን 568 ሺህ 348 መጽሐፍት ያስፈልገኛል አለ፡፡
ይህን ለማሳተምም ከ451 ሚሊየን 647 ሺህ ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የቢሮው የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና አቅርቦት ትግበራ ዳይሬክተር ናሽናል ድሪርሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡
በክልሉ መደበኛ በጀትና በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ የሣይንስ፣ ሒሳብና በአፍ- መፍቻ ቋንቋ የሚሠጡ የትምህርት ዓይነቶች ታትመው እየተሠራጩ ነው ብለዋል።
ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የታተሙት የትምህርት ዓይነቶችም የተማሪዎችን ዕድሜና የትምህርት ደረጃ ታሳቢ በማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአዲሱ የሥርዓተ- ትምህርት ዝግጅት አግባብ ሁሉም የትምህርት ዓይነቶች በቅርብ ጊዜ የዝግጅት ሂደታቸው መካሄዱን ጠቁመው፥ ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች በአንድ ጊዜ ለማሳተም የበጀት ዕጥረት ማጋጠሙን አስገንዝበዋል፡፡
በመሆኑም በቀጣይ አቅም በፈቀደ መልኩ መጽሐፍትን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
የኅትመት ዋጋ ንረት፣ የመጽሐፍት አቅርቦትና የተማሪ ቁጥር አለመጣጣም ተግዳሮት ሆብናል ያሉት አቶ ናሽናል፥ መጽሐፍትን ለተማሪዎችና መምህራን ተደራሽ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የየክፍል ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ለ2016 የትምህርት ዘመን ዝግጁ የሆኑት 247 ሺህ 336 ተማሪዎች ቢሆኑም÷ ከዚህ በፊት በጸጥታ ችግር ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች በ2016 ዓ.ም ሲከፈቱ የተማሪዎች ቁጥር እንደሚጨምር ጠቁመዋል፡፡
በትምህርት ዘመኑ በክልሉ÷ በቤኒሻንጉልኛ፣ ጉምዝኛ፣ አማርኛ፣ ሽናሽኛ፣ ጉዋመኛ፣ ኮሞኛ፣ ማኦኛ፣ ኦሮምኛ፣ ዓረብኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች ትምህርት ይሰጣል ነው ያሉት፡፡
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!