Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በክልሉ ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተመረጠ የአቮካዶ ተክል ተሸፍኗል- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ክልላችን በ2011 ዓ.ም የአቮካዶ ልማት ክላስተር ‹የአዳአ አቮካዶ ዲክላሬሽን› ከተጀመረ ወዲህ እስካሁን ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ የሆነ መሬት በአለም አቀፍ ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ባለው የተመረጠ የአቮካዶ ተክል ተሸፍኗል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡

ሀገራችን ትኩረት ሰጥተን ከሰራንባት ምርትን የምናፍስባት መሆኗን በተግባር አይተናል ብልዋል ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ደግሞ ትኩረት ሰጥተን በሰራንባቸው እንደ አቮካዶና ሌሎች አትክልትና ፍራፍሬዎች ምቹ የሆነ የአየር ጠባይ ያላትና የምንፈልገውን የምርት ብዛት ማምረት እንደምንችል በሚገባ ተረድተናል ነው ያሉት አቶ ሽመልስ።

በዚህም የምግብ እህልን ምርትና ምርታማነት በእጥፍ በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ለውጭ ገበያ የሚውሉ እንደ አቮካዶ ያሉ ምርቶችን ትኩረት ሰጥተን እየሰራ ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ በተጀመረው ስራም ትልቅ ስኬት አግኝተናል ብለዋል፡፡

እንደ ክልልም በ2011 ዓ.ም የአቮካዶ ልማት ክላስተር ‹የአዳአ አቮካዶ ዲክላሬሽን› ከተጀመረ ወዲህ እስካሁን ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ የሆነ መሬት በአለም አቀፍ ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ባለው የተመረጠ የአቮካዶ ተክል መሸፈኑን ነው የገለፁት።

የአቮካዶ ምርትን በማምረት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሀገራችን የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለመጨመር እየሰራን እንገኛለን ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ በአቮካዶ ምርት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ከፍተኛ ገቢ በማግኘት በኢኮኖሚ መሻሻል ውስጥ የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ አመላክተዋል፡፡

Exit mobile version