አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንታዊ ክርክር ላይ እንደማይቀርቡ ገልፀዋል፡፡
መንበረ ስልጣናቸውን ለጆ ባይደን አስረክበው ከነጩ ቤተ መንግስት ከተሰናበቱ በኋላ በተለያዩ ጉዳዮች ሲወንጀሉ የቆዩት የ77 ዓመቱ አዛውንት ሪፐብሊካን ፓርቲን በመወከል ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ ቀደም ሲል ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡
በቅርብ ጊዜ በተደረገ የህዝብ አስተያየትም ፕሬዚዳንቱ በ2024 በሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሪፐብሊካን እጩ ለመሆን ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በፓርቲው የፕሬዚዳንትነት ተቃናቃኛቸው የሆኑት የፍሎሪዳው ገዥ ሮን ዴሳንቲስ ሲሆኑ ከህዝብ በተሰበሰበ አስያየት ትራምፕ 62 በመቶ የፓርቲውን እጩነት ግምት ሲያገኙ ሮን ዴሳንቲስ ደግሞ 16 ፐርሰንት አግኝተዋል፡፡
ይሁን እንጂ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ በዚህ ወር በሚካሄደው የሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሬዚዳንታዊ ክርክር እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል፡፡
ትሩዝ በተባለው የግል ማህበራዊ ትስስር ገፃቸው “እኔ ማን እንደሆንኩ እና ምን አይነት የተሳካ የፕሬዚዳንትነት ጊዜ እንዳሳለፍኩኝ አሜሪካውያን ያውቃሉ” ብለዋል፡፡
የመጀመሪያው የሪፐብሊካን ክርክር ከነገ በስቲያ የሚካሄድ ሲሆን የመጀመሪያው ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ደግሞ በቀጣዩ ዓመት ጥር 15 ጀምሮ የሚካሄድ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ከ2017 እስከ 2021 ድረስ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ማገልገላቸው ይታወቃል።