Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለክልሉ ህዝብ የጋራ ተጠቃሚነት በትኩረት እንደሚሰራ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተራራቁ አስተሳሰቦችን ወደ አንድ በማምጣት ለክልሉ ህዝብ የጋራ ተጠቃሚነት በትኩረት እንሰራለን ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ውይይት በቡታጅራ ከተማ እየተካሔደ ነው፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፥ ክልሉ ሲቋቋም በነበረው የምክር ቤት ጉባኤ ልዩ ልዩ አዋጆችን በማጽደቅ ለበርካታ ዓመታት የነበሩ የህዝብ ጥያቄዎችን ምላሽ መስጠት ተችሏል፡፡

መንግስት ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠቱን ተከትሎ በክልሉ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን መግለጻቸውንም አቶ እንዳሻው አብራርተዋል።

እስከ ህዳር 2016 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ የሚቆይ የ100 ቀን እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱንም ገልጸዋል።

በእቅዱ የክልል ቢሮዎችን በተሟላ መንገድ ወደ ስራ ማስገባት፣ ዞኖች ልዩ ወረዳዎች እና ወረዳዎችም ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ይሰራል ብለዋል።

በ90 ቀናት እቅዱ በክልሉ የህዝብን ፍላጎት በመለየት እና በልማት ስራ በንቃት በማሳተፍ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራም መገለጹን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version