Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቀድሞ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አብዲ መሃመድን ጨምሮ 26 ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አብዲ መሃመድ ኡመርን ጨምሮ 26 ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል፡፡

ብይኑን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ-ሽብርና የሕገ-መንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

መደበኛ ችሎቱ ለተፋጠነ ፍትሕ አሰጣጥ ይረዳ ዘንድ በልዩ ሁኔታ በመሰየም ነው ዓቃቤ ሕግ ያሰማውን የምስክር ቃል መርምሮ ዛሬ ብይን የሰጠው።

በተከሳሾቹ ላይ ጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም በዓቃቤ ሕግ ቀርቦ በነበረ የክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው በሰኔና ሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም ውስጥ ባሉት ቀናቶች በሶማሌ ክልል ውስጥ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ የጦር መሳሪያ እንዲያነሳ እርስ በርስ ግጭት እንዲነሳ ለማድረግ በማሰብ ”ሄጎ” በሚል ስያሜ የሚታወቁ ወጣቶችን በማደራጀት ግጭት እንዲነሳ በማድረግና በግጭቱ ምክንያት የ59 ሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ ማድረጋቸው ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም በ266 ሰዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት እንዲደርስ፣ ወደ 412 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የመንግስት የግለሰብ ንብረቶች እንዲወድሙ፣ የእምነት ተቋማት እንዲቃጠሉ ፣ሴቶች እንዲደፈሩና እና በርካታ የከተማው ነዋሪ እንዲፈናቀል ተደርገዋል በማለት ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ ተደራራቢ ክስ ማቅረቡ ይታወሳል።

ተከሳሾቹ የክስ ዝርዝሩ ከደረሳቸው በኋላ ወንጀሉን አልፈጸምንም ብለው የሰጡትን የዕምነት ክሕደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ፍርድ ቤቱ ለዓቃቤ ሕግ ካስመዘገባቸው 213 ምስክሮች ውስጥ የ81 ምስክሮችን ቃል በተለያየ ጊዜ ማዳመጡ ተመላክቷል፡፡

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ የቀድሞ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አብዲ መሃመድ፣ የቀድሞ ሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ፈርሐት ጣሂር ፣ የበርከሌ ዞን ፖሊስ አዛዥ አብዱላሃ አህመድ ኑርን ጨምሮ 26 ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ከነዚህ ተከሳሾች መካከል 3ኛ፣ 5ኛ ፣ 7ኛ፣ 11ኛ እና 18ኛ ተከሳሾች የቀረበባቸው የክስ ድንጋጌ አንቀጹ ተቀይሮ በአንቀጽ 239 እና በአንቀጽ 257 መሰረት ነው እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠው።

በአጠቃላይ ተከላከሉ ከተባሉ 26ቱ ተከሳሾች መካከል 10ሩ ችሎት የተገኙ ሲሆን÷ ቀሪዎቹ 16ቱ ተከሳሾች ግን በሌሉበት እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል።

በዚሁ መዝገብ የተካተቱ ሌሎች 9 ተከሳሾች በሌሉበት፤ 7 ተከሳሾች ደግሞ ባሉበት ባጠቃላይ 16 ተከሳሾች በተከሰሱበት ድንጋጌ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል።

ሌላኛው የተከሰሰበት አንቀጽ ተቀይሮ በአንቀጽ 239ና በአንቀጽ 257 መሰረት እንዲከላከል ብይን የተሰጠው 3ኛ ተከሳሽ የቀድሞ የዳያስፖራ ቢሮ ኃላፊ አብዱረዛቅ ሰህኔ፤ የተቀየረው አንቀጽ ዋስትና የማያስከለክል በመሆኑ 30 ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ ከስር እንዲፈታ ታዝዟል።

ባሉበት ጉዳያቸው እየታዩ ያሉና እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠባቸው የቀድሞ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አብዲ መሃመድ ኡመርን ጨምሮ የ10 ተከሳሾችን የመከላከያ ማስረጃ ለመስማት ፍርድ ቤቱ ከሕዳር 3 ቀን እስከ ህዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ በሌሉበት እንዲከላከሉ ብይን በተሰጠባቸው 16 ተከሳሾችን ብቻ በሚመለከት ደግሞ ዓቃቤ ሕግ የማጠቃለያ የፍርድ ሀሳቡን በቀጣይ እንዲያቀርብ ታዝዟል።

ከአጠቃላይ 47 ተከሳሾች ውስጥ 17ቱ ባሉበት፣ 2የሚሆኑት ደግሞ በሌሉበት ጉዳያቸው የታየ ሲሆን÷ ቀሪ 5 ተከሳሾች በተለያዩ ምክንያቶች ከመዝገቡ ክሳቸው የመቋረጡ ተጠቅሷል።

ዓቃቤ ሕግ ከብይኑ በፊት 10 ገጽ በአማርኛ ቋንቋ የተተረጎመ ገላጭ ማስረጃ እንዲያዝለት አቤቱታ ያቀረበ ቢሆንም ማስረጃው ሒደቱን ጠብቆ የቀረበ ባለመሆኑ በችሎቱ ውድቅ ተደርጓል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version