Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ ለችግር የተጋለጡ ከ40 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚደርግ መርሃግብር ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ለችግር የተጋለጡ ከ40 ሺህ በላይ ዜጎችን”የኔ ቤተሰብ”በሚል ተጠቃሚ የሚሆኑበት መርሀግብር ይፋ ሆነ።
 
በድር ፋውንዴሽን የተባለ አገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅት አማካኝነት”የኔ ቤተሰብ” በሚል በኮቪድ -19 ወረርሽኝ ሳቢያ ለከፋ ችግር የተጋለጡ ከ40 ሺህ በላይ ዜጎችን ከለጋሽ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ጋር በማስተሳሰር ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችል መርሀግብር በዛሬው ዕለት ይፋ ሆኗል።
 
የቤተሰብ ማስተሳሰር መርሃግብሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ኢንጂነር እንዳወቅ አብቴ ፣የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት ተጀምሯል ።
 
በመርሃግብሩ ኢንጅነር እንዳወቅ አብቴ እንደገለጹት በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ለጉዳት የሚዳረጉ ዜጎችን ለመደገፍ የመንግስት አቅም ብቻ በቂ አይደለም ብለዋል።
 
የበድር ፋውንዴሽን እና መሰል ግብረሰናይ ድርጅቶች የአቅማቸውን ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን በመወጣት እና ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመደገፍ ይህንን የችግር ጊዜ ለማለፍ መረባረብ እንዳለበት ኢንጅነር እንዳወቅ ጥሪ አቅርበዋል ።
 
የበድር ፋውንዴሽን መስራች እና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር በድሩ ሁሴን በበኩላቸው በእስካሁን በኔ ቤተሰብ ትስስር 700 ለሚሆኑ ቤተሰቦች ለአንድ ወር የሚሆን የምግብ ፍጆታ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን 300 የሚሆኑት ደግሞ ለቀጣዩ ሶስት ወራት ድጋፍ የሚያደርጉላቸው ቤተሰቦች ማገናኘት መቻሉን ገልጸዋል።
 
ፋውንዴሽኑ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ድረ-ገጽ አማካኝነት ባሰባሰበው የገንዘብ ድጋፍ በአራዳ ክፍለ ከተማ ለሚኖሩ 150 አቅመ ደካሞች ለእያንዳንዳቸው 2 ሺህ ብር ግምት ያለው የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ኢንጅነር በድሩ መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።
 
”ቤተሰብ ዶት ኮም” በሚል በተከፈተው ድረ-ገጽም ለችግር የተጋለጡ ቤተሰቦችን መርዳት የሚፈልጉ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ግለሰቦችም ይሁን ተቋማት እንዲሁም በጎ አድራጊዎች የሚችሉትን ድጋፍ እንዲያደርጉ ስራ አስኪያጁ ጠይቀዋል።
Exit mobile version