አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ በስደት ወቅት የሚጠፉ ሰዎችን የተመለከተ የከፍተኛ ኃላፊዎችና የተለያዩ ባለደርሻ አካላት መድረክ በአዲስ አበባ አፍሪካ ሕብረት አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡
መድረኩ “በአፍሪካ የሚጠፉ ስደተኞችን ጉዳይ ምላሽ መስጠት፤ ከፖሊሲ እስከ እርምጃ” በሚል ሐሳብ ነው እየተካሄደ ያለው።
በውይይቱ ላይ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ቁልፍ ተቋማትና የስራ ክፍሎች ኃላፊዎች፣ የሕብረቱ አባል አገራት ተወካዮች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ የለጋሽ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የስደተኞች ጉዳይ ተዋናዮች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በመድረኩ በስደት ወቅት የሚጠፉ ሰዎችን ለመከላከልና ሰብዓዊ ክብራቸው እንዲጠበቅ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት እንደደረግ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራትና ተቋማት የሚጠፉ ስደተኞችና ቤተሰቦቻቸው የሚገጥሟቸው ፈተናዎች
መፍትሔ ለማበጀት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክረ ሐሳቦች እንደሚቀርቡም ተመላክቷል።
የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ እስከ አሁን ባደረገው ምዝገባ ከአፍሪካ በመነሳት ወደ አውሮፓና የባህረ ሰላጤ አገራት ለመግባት የተነሱ 64 ሺህ ዜጎች ጠፍተው የገቡበት አለመታወቁን ገልጿል።
የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይ ኦ ኤም) በፈረንጆቹ ከ1996 ጀምሮ በዓለም በስደት ይጓዙ የነበሩ 75 ሺህ ሰዎች መሞታቸውን ጠቅሶ÷ ከእነዚህ መካከል ከ40 ሺህ በላይ የሞቱት በፈረንጆቹ ከ2014 በኋላ መሆኑን አመልክቷል።
በፈረንጆቹ ከ2013 ጀምሮ በሜዲትራኒያን በኩል ሲጓዙ የነበሩ 23 ሺህ ሰዎች የጠፉ ሲሆን÷ በስደት ወቅት የሚጠፉ ሰዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት መኖሩ ተገልጿል።
የአፍሪካ ሕብረት ለጉዳዩ መፍትሔ ለማበጀት በፈረንጆቹ 2021 በስደት የሚጠፉ ዜጎችና በቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሰውን ተጽእኖ መከላከልን አላማ ያደረገ ‘ACHPR 486’ የተሰኘ የውሳኔ ሀሳብ አጽድቋል።
መድረኩን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን፣ ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚ ቴና በአዲስ አበባ የስዊዘርላንድ ኤምባሲ በጋራ ማዘጋጀታቸው ታውቋል።

