Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በጋምቤላ ከተማ ህዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ህዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ በጋምቤላ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በክልሉ ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ በየደረጃው የተካሄደው ህዝባዊ የውይይት መድረክ ማጠቃለያ ኮንፈረንስ ነው አሁን እየተካሄደ የሚገኘው።

በኮንፈረንሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሀይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች እየተሳተፉ ነው፡፡

በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ÷ መንግስት የዜጎችን ሰላም የማረጋገጥና የህግ የበላይነትን የማስፈን ሥራዎችን በተጠናከረ መንገድ ይሰራል ብለዋል፡፡

በፓርቲ እና በመንግስት ደረጃ በተደረገው ግምገማ በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር መንግስት ህዝቡን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ የልማት ስራዎችን ማከናወን አለመቻሉ ተግዳሮት እንደነበር አንስተዋል፡፡

ዋናው የችግሩ ባለቤት አመራሩ መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳደሩ ÷በቀጣይ ከዚህ ችግር ለመውጣት ያስችል ዘንድ ከክልል እስከ ወረዳ ባሉ አእና ሀላፊነታቸውን ባልተወጡ አመራሮች ዘንድ ርምጃ እንደሚወሰድ አብራርተዋል።

በተፈጠረው ግጭት ውስጥ የተሳተፉ አካላት በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ እና የማያዳግም የእርምት እርምጃ የመውሰዱ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በክልሉ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር በመቀልበስ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉ የፀጥታ አካላት እንዲሁም አገር በቀልና አለም አቀፍ ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሳ አህመድ በበኩላቸው÷ የህዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነት በማጎልበት ሰላምን ለማስፈን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል።

የዜጎች በሰላም ወጥቶ የመግባት መብታቸውና ነፃነታቸው ሊጠበቅላቸው ይገባል ያሉት አቶ ሙሳ ÷ይህንንም ለማስጠበቅ የአካባቢው ማህበረሰብን ጨምሮ አመራሮችና የፀጥታ አካላት ሚና የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

የሰላም ኮንፈረንሱ ለተከታታይ ሁለት ቀናት የሚካሄድ መሆኑን ከጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version