አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተከናወኑ ስራዎች ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለፁ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አመራሮችና ሠራተኞች የተሳተፉበት የ2015 ዓ.ም የዘርፉ የስራ ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና የአዲሱ በጀት ዓመት የሴክተሩ ዋና ዋና ግቦችን ማሳካት በሚቻልበት ሂደት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በዚሁ ወቅት አቶ መላኩ አለበል÷ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዎችና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን የማምረት አቅም ከማሳደግ አንፃር ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እርስ በራሳቸው የገበያና የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ትስስር እንዲኖራቸው፣ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ የአምራቹን ግንዛቤ ከማጎልበትና በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በመደገፍ ረገድ የተሻለ ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል፡፡
የሀገር ውስጥና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከመሳብ አንፃር አበረታች ውጤት የተመዘገበበት የበጀት ዓመት መሆኑን ገልጸው÷ በዚህም የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 55 በመቶ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።
በተለይም ለውጭ ገበያ የሚሆኑ ምርቶችን ማሳደግ፣ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እንዲሁም በዘርፉ የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ አበረታች ውጤት የተገኘበት ዓመት ነበር ብለዋል።
በዚህም ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያላቸውን ገቢ ምርቶች በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉን አቶ መላኩ አመልክተዋል።
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ማሳካት የሚያስችል መሰረት መሆኑን ማሳያ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡