አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የአጋማሽ ጊዜ የስራ አፈፃፀም የማረጋገጫ መድረክ እየተካሄደ ነው።
መድረኩ በስትራቴጂው ከተካተቱት ውስጥ እስካሁን የተሰሩ ስራዎች፣ የቀሩ ስራዎች እና ስራዎች በእቅድ መሰረት ያልተሰሩበት ምክንያት መለየት እንዲሁም ግብዓት ማከል ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።
በኢ-ኮሜርስ፣ በዲጂታል ክፍያ፣ በዲጂታል መታወቂያ እና በደንብና ፖሊሲ ዝግጅት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸው በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፥ ከዜጎች ህይወት ጋር የተሳሰሩ እና ከፍተኛ የስራ እድል እና ሃብት ሊፈጥሩ የሚችሉ ተብለው የተለዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች በስትራቴጂው መካተታቸውን ተናግረዋል።
ግብርና፣ ቱሪዝም፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም በኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አስቻይነት የሚተገበሩ አገልግሎቶች በስትራቴጂው ቅድሚያ የተሰጣቸው ዘርፎች ናቸው ብለዋል፡፡
ለስትራቴጂው ተግባራዊነትም የሚመለከታቸው ተቋማት ትብብር ወሳኝ መሆኑን ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመድረኩ ከ50 በላይ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ተወካዮች መሳተፋቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡