Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኮያንግፖኦክ ዩኒቨርሲቲ ለአዲስ አበባ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት እድል ለመስጠት ተስማማ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኮያንግፖኦክ ዩኒቨርሲቲ የተሻለ ውጤት ለሚያስመዘግቡ ለአዲስ አበባ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት እድል ለመስጠት ተስማማ።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በደቡብ ኮሪያ ቹንቾን ከተማ ከሚገኘው ታዋቂው ኮያንግፖኦክ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኪም ሂዎን ያንግ ጋር ተወያይተዋል::

በውይይታቸውም÷ በሁለቱ እህት ከተሞች መካከል በተደረሰው ስምምነት መሰረት የከንቲባ ነፃ የትምህርት እድል ፕሮግራም ማመቻቸት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ መክረዋል፡፡

ኮያንግፖኦክ ዩኒቨርሲቲ መስፈርት ለሚያሟሉና የተሻለ ውጤት ለሚያስመዘግቡ የአዲስ አበባ ተማሪዎች በከንቲባ የተሰየመ ነፃ የትምህርት እድል ለመስጠት ተስማምቷል::

የከንቲባ ነፃ የትምህርት እድል የከተማ አስተዳደሩ የአዲስ አበባ እህት ከተሞች ውስጥ ከሚገኙ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ለሚገኙ በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ለሚያስመዘግቡ ተማሪዎች የነፃ የትምህርት እድል ለመስጠት በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተጀመረ እንቅስቃሴ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ለከተማዋ ተማሪዎች መልካም እድል እንደሚፈጥርም ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ÷የሁለቱን ከተሞች የረዥም ዘመን ወዳጅነትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ የደቡብ ኮርያ ቹንቾን ከተማ ስኬታማ የስራ ጉብኝታቸውን አጠናቅቀው ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸው ተገልጿል፡፡

Exit mobile version