አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የምታከናውነው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የአፍሪካ ኅብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚና የዘላቂ አካባቢ ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ ተናገሩ።
ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የምታከናውነው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ወሳኝ እርምጃ ነው።
መርኃ ግብሩ ኢትዮጵያ በራሷ ተነሳሽነት ያለምንም የውጭ ድጋፍ የምታከናውነው መሆኑን ገልጸው ይህም አገሪቱ ለዘርፉ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
ድርቅንና የመሬት መንሸራተትን ለመከላከልም ትልቅ ሚና እንዳለው መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
መርኃ ግብሩ የአፍሪካ ኅብረት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ያወጣውን “ግሬት ግሪን ዎል” የተሰኘውን ስትራቴጂ የሚደግፍ መሆኑንም አንስተዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ሁነኛ መፍትሄ በመሆኑ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ከኢትዮጵያ ልምድ ሊቀምሩ ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የምታከናውነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረው ለዚህም ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
በመጪው ሰኞ በኬንያ ናይሮቢ ለሦስት ቀናት የሚቆይ አህጉራዊ የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ እንደሚካሄድ የአፍሪካ ኅብረት ገልጿል።
በዚህ ጉባኤ የአየር ንብረትን ለመከላከል የአፍሪካ አገራት በጋራ ድምጻቸውን የሚያሰሙበትና የጋራ አቋም የሚይዙበት እንደሚሆን ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።
በጉባኤው ከዚህ ቀደም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የተገቡ ቃል-ኪዳኖች ተግባራዊ ለማድረግ የጋራ መግባባት ላይ እንደሚደረስም አስረድተዋል።
በተለይም አፍሪካ የአየር ንብረትን ለመከላከል የውጭ ድጋፍ ላይ ያላትን ጥገኝነት በማላቀቅ በራስ አቅም መፍትሄ ማምጣት በሚቻልበት መንገድ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።