አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ መስዋዕትነት የሚከፍሉ ናቸው ሲሉ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡
ጳጉሜ 2 የመስዋዕትነት ቀን “በመስዋዕትነት የምትፀና ሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ቅጥር ግቢ በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከበረ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሠ፣ ጀኔራል መኮንኖች፣ የፌዴራል የፀጥታ ከፍተኛ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመድረኩ ተገኝተዋል።
አቶ ተመስገን በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ከኢትጵያ ህዝብ አብራክ የተገኙና ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ መስዋዕትነት የሚከፍሉ ናቸው ብለዋል፡፡
መስዋዕትነት ማለት አንድን ከፍ ያለ ዓላማ ለመፈፀም ሲባል የራስን ነገር ማጣት ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለጸጥታና ደህንነት አባላትና ለኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ቀደምት አባቶች ጠላትን ድባቅ እየመቱ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ለትውልዱ ማስረከባቸውን አስታውሰው፤ አባቶች ያለ አንዳች ዘመናዊ መሳሪያና ትጥቅ ወራሪዎችን እምቢኝ በማለት ከፍ ያለ መስዋዕትነት በመክፈል የሀገርን ነፃነት ማስጠበቃቸውን ተናግረዋል።
የትኛውም ሀገር በስጦታ አልተገኘም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በመስዋዕትነት ከሚገኙ ነገሮች ቀዳሚው ሀገር ነው በማለት ገልፀዋል፡፡
ትውልድ ሦስት ዓይነት መስዋዕትነት ለኢትዮጵያ እንደከፈለ ያነሱት አቶ ተመስገን፤ ሉዓላዊነቷን ለመጠበቅ፣ ሀገረ መንግስቷን ለማፅናት እና የተሸለ ሥርዓት ለመፍጠር ዋጋ ተከፍሏል ብለዋል፡፡
የሺህ ዘመናት ታሪኳ ኢትዮጵያ ልጆቿ በከፈሉት መስዋዕትነት እንዴት እራሷን ከባዕዳን ወራሪዎች እንደተከላከለች ያሳዩናል ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ራሷን ከቅኝ ገዢዎች ለመጠበቅ ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉ ልጆች ያሏት ሀገር ናት በማለት ገልጸው፤ ከባድ መስዋዕትነት የተከፈለባት ታላቅ ሀገር መሆኗን አስታውሰዋል።
በታምራት ቢሻው