አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቡድን 20 አባል ሀገራት ለአፍሪካ ህብረት ከአውሮፓ ህብረት እኩል ቋሚ የአባልነት መቀመጫ እንዲሰጥ ተስማምተዋል።
ውሳኔው 55 አባል ሀገራት ላሉት አህጉራዊ አካል የአፍሪካ ህብረት በተጋባዥ ዓለም አቀፍ ድርጅትነት ከተሰየመበት ወጥቶ ከአውሮፓ ህብረት እኩል ተመሳሳይ ደረጃ ይሰጣል ነው የተባለው።
የቡድን 20 ተለዋጭ ፕሬዚደንት የሆነችው የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ሌሎች መሪዎች የአፍሪካ ህብረትን በቡድኑ አባልነት እንዲቀበሉ ባለፈው ሰኔ ወር በደብዳቤ ማሳሰባቸው ተጠቅሷል።
በአሁኑ ጊዜ የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ 19 ሀገራትን ያካተተው ቡድን 20 አባል ሀገራቱ ከዓለም አቀፉ የሀገር ውስጥ ምርት 85 በመቶውን ሲይዙ ከ75 በመቶ በላይ የዓለምን ንግድና ሁለት ሶስተኛውን የዓለም ህዝብ መያዛቸው ተገልጿል።
የቡድን 20 አባል የሆነችውና የአፍሪካ ህብረት መቀላቀልን የምትደግፈው ደቡብ አፍሪካ ከዴልሂው የመሪዎች ጉባኤ ቀደም ብላ አስተያየት ከመስጠት መቆጠቧ ተነግሯል።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ቃል አቀባይ ቪንሴንት ማግዌንያ “ጉባኤው ይፋዊ ማስታወቂያ እስኪያወጣ ድረስ አስተያየት አንሰጥም” ማለታቸውን ሰንዴይ ታይምስ ዘግቧል፡፡
እንደ ጀርመን፣ ብራዚል፣ ደቡብ አፍሪካና ካናዳ ያሉ ሀገራት የአፍሪካ ህብረት አባልነትን የደገፉ ሲሆን÷ የቡድን 20 መሪዎች ውሳኔውን በጉባዔው ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የአፍሪካ ህብረት አባልነት መደበኛ የሚሆነው በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት ብራዚል የቡድኑን መሪነት ከህንድ ስትረከብ እንደሆነ ዘገባው አያይዞ ገልጿል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!