Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአፍሪካ የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሀገራት በትብብር ሊሰሩ ይገባል- አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሀገራት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

የአፍሪካ ህብረት ከተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት ጋር በመሆን በአፍሪካ ሰላምና ልማትን ማስቀጠል የሚያስችል ቀጣናዊ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

በመድረኩም ግጭትና የሰላም እጦት በተለይ ታዳጊ የአፍሪካ ሀገራትን ኢኮኖሚ በብርቱ እንደሚጎዳ ተመላክቷል፡፡

በአፍሪካ የሚሰሩ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ፍትሓዊ ተጠቃሚነትን ካላረጋገጡ እስከ 2030 ተጨማሪ 100 ሚሊየን ሥራ አጥ ዜጎች ይፈጠራሉ ብሏል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን በዚሁ መድረክ እንዳሉት÷ ዘላቂ የልማት ግቦችን በማሳካት የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ግጭትና ድህነትን ማስወገድ ይገባል፡፡

ልማት የተሟላ የሚሆነው ማህበረሰቡን በፍትሃዊነት ተጠቃሚ ማድረግ ሲችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ሰላም፣ ልማትና ሰብዓዊ መብቶች የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ገልጸው÷በእነዚህ ሶስቱ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ አንድነት መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የህዝቡን ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ለመመለስና በመላ ሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በትኩረት እየሰራ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ተርክ በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት÷ያለ ዘላቂ ሰላም የሰብዓዊ መብት በሚፈለገው ደረጃ ማረጋገጥ እንደማይቻል ጠቁመዋል፡፡

የሰብዓዊ መብቶችን ያለ ገደብ ለማክበር ሀገራት ስር ነቀል ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የኢኮኖሚ መሰረተ ልማቶችን መገንባትና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ተደራሽ ማድረግ አለባቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version