አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረር ከተማ ሰሞኑን ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ ንብረት ከወደመባቸው ነጋዴዎች ጋር ውይይት ተካሄደ።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የሐረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዱልጀባር መሀመድ÷ በፎረንሲክ ባለሙያ አማካኝነት የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በደረሰው የእሳት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ነዋሪዎች ለማቋቋም ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።
በአደጋው የተጎዱ ነጋዴዎችም ተመልሰው እንደሚቋቋሙ ያረጋገጡት ሃላፊው በዚህ ላይም ኮሚቴው የአጭር እና የረጅም ጊዜ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ነጋዴውም በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጨውን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ማዳመጥ እንደለሌበት እና ተግባሩንም ማውገዝ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የክልሉ መንግስትም ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር የጀመረውን የልማት ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ አብዱልጀባር አረጋግጠዋል።
በሐረር ከተማ በተለምዶ “ታይዋን” በተባለው የገበያ ስፍራ ዻጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሰዓት የተከሰተ ድንገተኛ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት ማስከተሉ ይታወሳል።