Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ፈረንሳይ በተለያየ ጣዕም የሚዘጋጁ የኤሌክትሮኒክስ ሲጋራን ልታግድ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፈረንሳይ በተለያየ ጣዕም የሚዘጋጁ የኤሌክትሮኒክስ ሲጋራ ምርቶችን ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ለማድረግ የሚያስችል እቅድ ማውጣቷን አስታውቃለች፡፡

በሀገሪቱ በከፍተኛ ዋጋ የሚሸጡት እነዚህ የሲጋራ ምርቶች ታዳጊዎችን ወደ ሱስ መክተታቸውና ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላ የሚጣለው የሲጋራ ቅሪት የሚያስከትለው የአካባቢ ብክለት ለእገዳው ምክንያት መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡

የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤልዛቤት ቦርን እንደገለፁት እርምጃው መንግስት ቀደም ሲል ያቀደው የፀረ-ሲጋራ ዘመቻ አንድ አካል ነው ብለዋል፡፡

ይህ እቅድም በተያዘው ዓመት መጨረሻ አካባቢ ተግባራዊ እንደሚደረግ ነው ያመላከቱት፡፡

ጀርመን፣ ቤልጂየም እና አየርላንድን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትም በእነዚህ የሲጋራ ምርቶች ላይ  ተመሳሳይ እገዳ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

የሲጋራ አምራቾች የተለያየ ጣዕም ያላቸውን የሲጋራ ምርቶች እያመረቱ ለገበያ ማቅረባቸው ህፃናት በቀላሉ ለሱስ ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓል እየተባለ ነው።

እነዚህን የሲጋራ ምርቶች የሚቃወሙ ተሟጋቾች ደግሞ አምራቾች በተለይም ታዳጊዎችን ማዕከል አድርገው ምርቶቹን ያሰራጫሉ ሲሉ ይወነጅላሉ።

እነዚህ የሲጋራ ምርቶች በታዳጊዎችና ወጣቶች ተመራጭ በመሆናቸው በሂደት ከፍተኛ የሲጋራ ሱስ ተጠቂ የማድረግ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑንም ነው የሚገልጹት።

ከዚህ አንጻርም አስፈላጊው የእገዳ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ማለታቸውን ቢቢሲ እና ሜትሮ አስነብበዋል።

እነዚህን የሲጋራ ምርቶች እድሜያቸው ከ13 እስከ 16 አመት የሚደርሱ ቢያንስ 13 በመቶ ታዳጊ ህጻናት የሚጠቀሟቸው ሲሆን በአብዛኛው በ11 እና 12 አመት የእድሜ ክልል ላይ ሆነው እንደሚጀምሩም የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ።

Exit mobile version