አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከነገ ጀምሮ የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት መስጠት እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በሰጡት መግለጫ÷ የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ በክልሉ በቋራ ወረዳ ሐምሌ 7 ቀን 2015 ዓ.ም መከሰቱን አስታውቀዋል፡፡
ለጤና ባለሙያዎች በተሰጠው ስምሪት መሰረት የበሽታውን መስፋፋት መግታት ቢቻልም÷ በበሽታው የተያዙ ሰዎች በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በመሄዳቸው በሽታው ወደሌሎች አካባቢዎችም ሊስፋፋ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በዚህም በሽታው ጎንደር እና ባህር ዳርን ጨምሮ በክልሉ በ28 ወረዳዎች ተከስቷል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
አሁን ላይም በ11 ወረዳዎች በሽታው መኖሩን ጠቁመው÷ ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ጎንደር እና ባህር ዳር ከተሞችን ጨምሮ በዘጠኝ ወረዳዎች ከአንድ አመት በላይ ለሆናቸው ለሁሉም ሰዎች ከነገ ጀምሮ በመተመረጡ የጤና ተቋማት የኮሌራ በሽታ ክትባት ይሰጣል ብለዋል፡፡
ከክትባቱ በተጓዳኝ በሽታው እንዳይዛመት ሌሎች የመከላከያ ስልቶችን መተግበር እንደሚገባ አሳስበው÷ ክትባቱ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች በተለይም በምእራብ አማራ የወባ በሽታ እንደተከሰተ ገልጸዋል፡፡
የመከላከል ስራ እየተሰራ ቢሆንም የታማሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
ከወቅታዊ የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ የወባ መድሃኒት እጥረት ማጋጠሙንም ነው የተናገሩት፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!