Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ሌብነትን በቁርጠኝነት እንታገላለን – የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀብት እንዳይባክና ሌብነትን በቁርጠኝነት በመታገል ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግሩ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።

ለፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ”ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀው የመጀመሪያ ዙር ስልጠና በአዳማ ከተማ እየተሰጠ ነው።

አመራሩ የኢትዮጵያን እምቅ ሀብቶች በአግባቡ በማወቅ ለማልማትና የሀብት ብክነት እንዳይኖር በቁጭት እንዲነሳ ማድረግ የስልጠናው ዓላማ መሆኑን በስልጠናው እየተሳተፉ የሚገኙ አመራሮች ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለሁሉም ዜጎች የምትመች አድርጎ በመገንባት በአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ተግቶ መስራት፣ ሌብነትን በቁርጠኝነት በመታገል የሀብት ብክነት እንዳይኖር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

በተለይም ሳይታረስ ጦሙን የሚያድር መሬትን ወደ ልማት የማስገባት፣ የውሃ ሀብትን በአግባቡ የመጠቀም፣ ማዕድናትን የማልማት ስራን ጨምሮ የተለያየ ስራ በስፋት እየተሰራ ስለመሆኑም አስገንዝበዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት የታቀዱ የልማት ሥራዎችን በአዲስ አስተሳሰብ በፍጥነትና በጥራት ለማሳካት እንሰራለን ያሉት ከፍተኛ አመራሮቹ÷ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀገራዊ ኃላፊነታችንን በአግባቡ እንወጣለን ብለዋል፡፡

ችግሮችን ወደ ድል በመቀየር ኢትዮጵያ ያላትን አቅም አሟጦ በመጠቀም ለውጥን ማረጋገጥ እንደሚቻል ከስልጠናው መገንዘባቸውንም ገልጸዋል፡፡

ስልጠናው አመራሩ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት እንዲሰራ አቅም የሚፈጥር ስለመሆኑም አመላክተዋል፡፡

ሀብት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ያህል እንዳይባክን ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ የአመራሩ ወሳኝ ሚና መሆኑንም ነው ስልጠናው ተሳታፊዎች የተናገሩት፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version