አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪዎች ማህበር አባላት ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገለፁ፡፡
የማህበሩ አባላት የልምድ ልውውጥ ማድረግ የሚያስችል ገብኝት በኢፌዴሪ አየር ኃይል አድርገዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የአየር ኃይል አዛዥ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፥ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአቪዬሽን ሳይንስ የሚመራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አየር ኃይል ከየትኛውም የፖለቲካ፣ የዘር፣ የሀይማኖት እና ሌሎች ተልዕኮዎች ውጭ ነው ያሉት ዋና አዛዡ÷ ተቋሙ በገለልተኝነት የተሠጠውን ተልዕኮ የሚፈፅም ነው ብለዋል።
በመሆኑም የአየር መንገዱ አብራሪዎችም ይህንን ከግምት በመውሰድ ለየትኛውም አፍራሽ ተልዕኮ ቦታ ባለመስጠት ለሀገራቸው ክብር ሲሉ ኃላፊነታቸውን በተግባር ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ካፒቴን ሚካኤል ስንታየሁ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ አየር ሀይል እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሀገራችን ካሉ ስመ ገናና ተቋማት መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በተቋማቱ በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትብብር በመስራት ሀገራቸውን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማሻገር ይሰራሉ ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡