Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ጎብኚዎች የሚሳተፉባቸውን ክዋኔዎች ማስፋት እንደሚገባ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ጎብኚዎች የሚሳተፉባቸውን ክዋኔዎች ማስፋት እንደሚገባ የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ሣይንስና ባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ ባላት ተፈጥሯዊ፣ ባሕላዊና ኃይማኖታዊ የቅርስ ሃቶችና የቱሪስት መዳረሻዎች የውጭ ጎብኝዎችን ቀልብ የመሳብ አቅም አላት፡፡

በቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አለማየሁ ጌታቸው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር የቱሪስት መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል፡፡

በቆይታቸው እንዳሉትም፥ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ጎብኚዎች የፈለጉትን አገልግሎት እንዲያገኙና መዳረሻ ቦታዎችን እንዲያውቁ የሚያስችል በቂ መረጃ እንደሚያስፈልግ ነው የጠቀሱት፡፡

በዚህም የተለያዩ መረጃዎችን ቀድሞ በመስጠት ጎብኚዎች ለሚጎበኙትና ስለሚያስፈልጋቸው ነገር ቀድመው እንዲዘጋጁ እየተደረገ ነውም ብለዋል፡፡

ጎብኚዎች ገንዘባቸውን በተለያዩ አገልግሎቶች ላይ ፈሰስ አድርገው እንዲሄዱ የቆይታ ጊዜያቸውን ማራዘም አማራጭ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ የሚገኙ መዳረሻዎች ጎብኚዎች የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ በር እንደሚከፍቱም ነው የተናገሩት፡፡

የቆይታ ጊዜያቸው ሲራዘም ደግሞ ጎብኚዎች የሚሳተፉበትን ክዋኔዎችን ማስፋትና አገልገሎቶችን ከፍ ማድረግ እንደሚጠይቅም አንስተዋል፡፡

በዚህም የሚመለከታቸው አካላት በዚህ ዙሪያ ተቀራርበው እንዲሰሩ እየተደረገ እንደሚገኝም ሥራ አስፈጻሚው አክለው የገለጹ ሲሆን፥ ከቱሪዝም ኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ ያሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ እየተሰራ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡

በሌላ መልኩ የጸጥታ ችግር ተጽዕኖ ከሚያሳድርባቸው ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የጸጥታ ሁኔታ ላይ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች የጠራና ትክክለኛ መረጃ እንዲኖራቸውን ለማድረግ እየተሰራ ነውም ተብሏል፡፡

Exit mobile version