Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ 134 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ስራ ይገባሉ ተባለ

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት 134 የመስኖ ፕሮጀክቶችን ግንባታ በማጠናቀቅ ወደ ስራ እንዲገቡ ይደረጋል ሲል የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አየልኝ መሳፍንት እንደገለጹት÷ ባለፉት ዓመታት ተጀምረው ግንባታቸው በተለያየ ደረጃ ከሚገኙት 236 የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል የ134ቱን ፕሮጀክቶች ግንባታ በማጠናቀቅ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው።

ከእነዚሁ የመስኖ ፕሮጀክቶች ውስጥ በደቡብ ወሎ ሚሌ ኩትቻ፣ በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር የታችኛው ኳሽሚ፣ በደቡብ ጎንደር አጓት ውሃ፣ በሰሜን ሸዋ አዋሰ ከሰምና ሌሎች ግድቦች እንደሚገኙበት አመላክተዋል።

የቀሪዎቹን 102 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ደግሞ አሁን ካሉበት የአፈጻጸም ደረጃ ወደ ተሻለ ለማድረስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

በበጀት ዓመቱ የሚጠናቀቁ የመስኖ ፕሮጀክቶችም 8 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ በማልማት የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።

ለሁሉም የመስኖ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ከክልሉ መንግስት፣ ከዘላቂ ልማት፣ ከግብርና እድገት ፕሮግራምና ከሌሎች ድርጅቶች ከሚገኘው ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ በጀት መያዙንም አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የፌደራል መንግስት በራሱ ለሚያስገነባቸው ፕሮጀክቶች ተጨማሪ በጀት በመመደብ የሚያከናውን መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በክልሉ በመስኖ መልማት የሚችል ከ2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ቢኖርም እስካሁን ማልማት የተቻለው ከ10 በመቶ በታች እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

Exit mobile version