አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጋምቤላ ክልል ሰሞኑን ተከስቶ በነበረው የጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች የአይነት ድጋፍ አድርጓል።
በማህበሩ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቼንኮት ዴቪድ፥ ድጋፉ በጋምቤላ ከተማ እና በ5 ወረዳዎች አቅመ ደካሞችን ጨምሮ ከፍተኛ ጉዳት ላጋጠማቸው 475 እማዎራዎችና አባዎራዎች መደረጉን ገልጸዋል።
ከድጋፉ ውስጥ ብርድ ልብስ፣ የመኝታና የዝናብ መከላከያ ፕላስቲክ፣ የውሃ ጄሪካና የንጽህና መጠበቂያ ግብዓቶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
በጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከትናንት ጀምሮ ድጋፉን ማሰራጨት መጀመሩንና ለቀሪዎቹም ማከፋፈሉ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡
ቀደም ሲልም ተመሳሳይ ድጋፍ ለ725 እማዎራዎችና አባዎራዎች መደረጉን አስታውሰው÷ ማህበሩ ሰብዓዊ ድጋፉን በቀጣይም እንደሚያጠናክር መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ኡሞድ ኡሞድ በበኩላቸው ÷ ማህበሩ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለተጎዱ ፈጥኖ በመድረስ እያደረገ ላለው ሰብዓዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ጎርፍ ባስከተለው ችግር የተፈናቀሉ ወገኖችን የመደገፉ ተግባር በሌሎችም ተቋማት ተሳትፏቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡