Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የኢንኩቤሽን ማዕከል በቻይና ከፈተ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ከቻይና ዓለም አቀፍ የንግድ ትብብርና ትስስር ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ፕሮጀክት ኢንኩቤሽን ማዕከል በቻይና ከፈተ።

ማህበሩ ማዕከሉን የከፈተው በሁናን ግዛት ቻንግሻ ከተማ በቻይና-አፍሪካ የወጣቶች የኢኖቬሽንና ኢንተርፕረነርሺፕ ቤዝ ሃይ-ቴክ ዞን ላይ ነው።

ማዕከሉ በቻይናና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን የሚያበረታታ ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም በወጣት ስራ ፈጣሪዎች መካከል በኢኖቬሽን፣ በቴክኖሎጂና በስራ ፈጠራ ተቀናጅተው እንዲሰሩ እድል ይፈጥራልም ነው የተባለው፡፡

በስነስርዓቱ በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኢንቨስትመንትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዲፓርትመንት ምክትል ሀላፊ ይስሀቅ ሽመልስ÷ ስምምነቱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በንግድ ማስተዋወቅ ረገድ እድሎችን ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትየጵያ ስራ ፈጣሪ ማህበር ፕሬዚዳንት ሳሚያ አብዱልቃድር÷ ማህበሩ ስራ ፈጠራን ለማስተዋወቅ፣ ለመደገፍ ምቹ ስነምህዳር እንዲፈጠር በወጣት ስራ ፈጣሪዎች በፈረንጆቹ 2020 መቋቋሙን አስታውሰዋል፡፡

ማህበሩ ከሀገር ውስጥና ውጭ ካሉ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ፣ የልማት አጋር ተቋማት እንዲሁም ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራ ነው መባሉንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የቻይናዋ ሁናን ግዛት የንግድና ገበያ ቁጥጥር ቢሮ ተመራማሪና የዓለም አቀፉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ልውውጥ ማዕከል ዳይሬክተር ሊ ዌይሚን በበኩላቸው÷ ማዕከሉ በቻይና አፍሪካ የመጀመሪያ የወጣቶች ኢኖቬሽንና ስራ ፈጠራ ማዕከል ነው ብለዋል።

Exit mobile version