Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአፍሪካ ከንቲባዎች የሊደርሺፕ ኢኒሼቲቭ መድረክ ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከነገ ጀምሮ የአፍሪካ ከንቲባዎች የሊደርሺፕ ኢኒሼቲቭ መድረክ በአዲስ አበባ እንደሚያካሂድ ተጠቆመ።

የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እናትአለም መለሰ በሰጡት መግለጫ÷ ከተማዋ ከነገ ጀምሮ ዓለም አቀፍ፣ አሕጉር አቀፍ እንዲሁም አገር አቀፍ ልዩ ልዩ መድረኮች እንደምታስተናግድ አመልክተዋል።

መስከረም 24 እና 25 የአፍሪካ ከንቲባዎች የሊደርሺፕ ኢኒሼቲቭ መድረክ፣ ከ28 እና 29 የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም የልህቀት ማዕከልን ለማቋቋም የሚረዳ ዓለም አቀፍ የምክክር መድረክ እንዲሁም ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም የሀገር አቀፍ መሪዎች የልምድ ልውውጥ መድረኮች ይካሄዳሉ ብለዋል፡፡

የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም አበረታች ውጤት ማስመዝገብ የቻለ መሆኑን በመግለጽ አስተዳደሩ 9 ሺህ 500 ለሚሆኑ ሕጻናትና ወላጆች በከተማዋ አልሚ ምግብ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

መድረኮቹ በሁሉም ረገድ የተጀመሩ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጋራሞች እውቅና እንዲያገኙ ያስችላልም ማለታቸውን የከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

እንዲሁም ተሞክሮውን እንደ ሀገርና አህጉር በማስፋት አህጉራዊ ተቀባይነትን ለማጉላት የላቀ አስተዋጽኦም እንደሚኖረው ተመላክቷል፡፡

 

Exit mobile version