Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለኢንዱስትሪዎች የሚውል የጨው ግብዓት ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለምግብ፣ ለመጠጥ፣ ለኬሚካል እንዲሁም ለቆዳ ፋብሪካዎች እና ኢንዱስትሪዎች የሚውል በቂ የጨው ግብዓት ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ለኢንዱስትሪ ግብዓት በሚውል ጨው አቅርቦት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ውይይት ተካሂዷል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሐሰን መሐመድ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት÷ ጨውን በግብዓትነት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች በየዓመቱ ከ26 ሚሊየን 353 ሺህ በላይ ኩንታል ጨው ይፈልጋሉ።

ነገር ግን እየቀረበ ያለው ጨው 50 በመቶው ብቻ መሆኑን ገልጸው÷ ይህም ሀገሪቱ ካላት የጨው ሐብት ጋር ሲነጻጸር እየቀረበ ያለው በቂ አለመሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

የዘርፉ ፖሊሲዎች በአግባቡ አለመተግበራቸው፣ በጨው ፈላጊዎች እና አቅራቢዎች መካከል ያለው ትሥሥር አለመጠናከር፣ የአቅራቢዎች ቁጥር ውስን መሆን እንዲሁም ሕገ-ወጥ ደላሎች ለግብዓት እጥረቱ  ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

በአቅርቦት እጥረት ምክንያት በጨው ግብዓት የሚሰሩ ኢንዱስትሪዎች እንዳይስፋፉ እና በተለያዩ ፋብሪካዎች  የሚፈለገው ያህል  የሥራ ዕድል እንዳይፈጠር እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ችግሩን ለመፍታት ምቹ አሰራሮች እየተዘረጉ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው÷ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በመጠቀም በዘርፉ ያሉ የፋይናንስ፣ የአሰራር እና አቅርቦት ችግሮች እንዲፈቱ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ገልጸዋል።

የአቅርቦት ችግሩን ለመቅረፍ የጨው አምራች ማሕበራትን አቅም ማጎልበትም ሌላኛው መፍትሄ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version