አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሸገር ከተማ አስተዳደር በተያዘው በጀት አመት በ1 ቢሊየን ብር ወጪ ለማህበረሰቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት የሚውሉ አራት ፕሮጀክቶች ግንባታ እንደሚጀመር ተገለጸ።
የንጹህ ውሃ ፕሮጀክቶቹ ከሚጀመሩባቸው ቦታዎች መካከል በገፈርሳ ጉጄ ወረዳ፣ በጀሞ መልካ ናኖ ተራራ ስር ያለ አካባቢ ይገኝበታል።
የሸገር ከተማ የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈትቤት ኃላፊ አቦማ ደሬሳ (ኢ/ር) ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቁት÷ በገፈርሳ ጉጄ በ456 ሚሊየን ብር ወጪ 80 ከመቶ ማህበረሰቡን የንፁህ ውሃ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ የተጠና ፕሮጀክትን ወደ ስራ ለማስገባት በጨረታ ሂደት ላይ ነው።
በተመሳሳይ በሌሎችም የአርሶ አደር መኖሪያ ክፍለ ከተሞች የንፁህ ውሃ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ለማስገባት በጨረታ ሂደት ላይ መሆኑን አክለዋል።
ጽህፈት ቤቱ በበጀት አመቱ በአጠቃላይ ለማከናወን አስቀድሞ ያስጠናቸው 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የሚፈጁ 13 የውሃ ፕሮጀክቶች ያሉ ቢሆንም የሸገር ከተማ አስተዳደር በበጀት እጥረት ምክንያት ለአራቱ የውሃ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ በመስጠት በ1 ቢሊየን ብር በጀት ለማከናወን አቅዶ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።
አራት የንፁህ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ በአርሶ አደር ማህበረሰቡ የሚነሱ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ጥያቄዎችን ይፈታሉ ብለዋል።
በታሪክ አዱኛ