አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲከበር ከአባገዳዎችና ከሀደሲንቄዎች ጋር በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት ውይይት አካሄደ።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል÷በዓሉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የጋራ ግብረ-ኃይሉ በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡
በበዓሉ ላይ ብሔር ብሔረሰቦችና ቱሪስቶች የሚሳተፉበት በዓል እንደመሆኑ መጠን ከዋዜማው ጀምሮ በአዲስ አበባ የሆራ ፊንፊኔና በቢሾፍቱ ከተማ በሚከበረው የሆራ አርሰዲ ማጠናቀቂያ ድረስ ግብረ ኃይሉ ከአባገዳዎችና ሀደሲንቄዎች ጋር በመተባበር እንደሚሠራም ጠቅሰዋል፡፡
የፀጥታ ኃይሉ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱ የአዲስ ዓመትና የመስቀል ደመራ በዓላት በሰላም እንደተከበሩ ሁሉ የኢሬቻ በዓልም በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ ሥራውን እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
ለዚህም ከህዝብና መንግስት ጋር በመተባበር በዓሉ በሰላም እንዲከበር እናደርጋለን ማለታቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

