አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በየዘርፋቸው ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ የሚሰራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት÷ የምክር ቤቱ አባላት የሕዝብ ውክልና ሥራቸውን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
በመድረኩ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ የምክር ቤት አባላት በክልላቸው የነበረውን የውክልና ሥራ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተወካዮች ምክር ቤት አባል አብርሃም አለማየሁ (ዶ/ር) እንዳሉት ÷ በክልሉ ከሕዝቡ ጋር ስኬታማ ውይይት መደረጉንም ነው የተናገሩት።
በውይይቱ ለበርካታ ጊዜ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ የቆየው የአደረጃጀት ጥያቄ ምላሽ መሰጠቱ በህዝቡ ዘንድ ተስፋን መሰነቁን አረጋግጠናል ብለዋል።
ይሁን እንጂ የመሰረተ ልማትና ሥራ እድል ፈጠራ የሕዝቡ መሰረታዊ ጥያቄዎች መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
በምክር ቤቱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ተወካይ ዳውድ መሃመድ÷ ከሕዝቡ ጋር በነበረው ውይይት የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች መነሳታቸውን አስታውቀዋል።
ለአብነትም በክልሉ አዋሳኝ አካባቢዎች የነበሩ የጸጥታ ችግሮች መነሳታቸውን በመግለጽ አሁን ላይ ችግሩ በዘላቂነት እልባት እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በምክር ቤቱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተወካይ አልማዝ አሳሌ(ኢ/ር) በበኩላቸው ÷ ህዝቡ “ሊመለሱልኝ ይገባል” የሚላቸው ጥያቄዎች የመሰረተ ልማት፣ እንደ ትምህርትና ጤና ተቋማት ያሉ ማህበራዊ ጉዳዮች መሆናቸውን ለይተናል ብለዋል።
የአዲስ አበባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሙሉ ይርጋ ÷ የሰው ተኮር ፕሮጀክቶች አፈፃፀምና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሕዝቡ ዘንድ ቅቡልነት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር፣ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ መናር፣ የሕገ-ወጥ ደላሎች መብዛት እንዲሁም ሙስናና ብልሹ አሰራር እንዲፈቱ ሕዝቡ ማንሳቱን ም ነው ያነሱት።
የአማራ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ተስፋሁን ቦጋለከመብራት፣ ቴሌኮምና መንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ አንፃር የተመለሱ ጥያቄዎች መኖራቸውን ገልጸው ÷ የሰላምና ደኅንነት ሁኔታ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው ብለዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴዔታ መሰረት ሃይሌ÷የምክር ቤት አባላት ከወከሉት የማኅበረሰብ ክፍል ጋር የፊት ለፊት ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ሰላምና መልካም አስተዳደር፣ ግብርና፣ መሰረተ-ልማት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የፕሮጀክቶች አፈፃፀምና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ከሕዝቡ ጋር ውይይት መደረጉንም ነው የጠቆሙት።
በመሆኑም በተለይም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቃለሉ እንዲሁም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችሉ ተግባራት እንዲጠናከሩ ምክር ቤቱ ሃላፊነቱን ይወጣል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሕዝቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች በየዘርፋቸው ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ ምክር ቤቱ የክተትልና የቁጥጥር ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት፡፡