አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተለያዩ ተጠርጣሪዎች የተያዘን 16 ነጥብ 2 ኪሎ ግራም የኮኬይን ዕፆችን በመሰወር በሌላ ንጥረ ነገር ቀይሯል በተባለው የፌደራል ፖሊስ አባል ላይ ክስ ተመሰረተ።
የፌደራል ፖሊስ አባል በሆነው ረዳት ኢንስፔክተር ታምራት ታደሰ ለማ ላይ ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ተረኛ ወንጀል ችሎት ነው።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ተከሳሹን በቁጥጥር ስር አውሎ በጊዜ ቀጠሮ የወንጀል ምርመራ ሲያከናውንና ማስረጃዎችን ሲያጣራ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ÷ የምርመራ መዝገቡን ከፖሊስ ተረክቦ ማስረጃዎችን በማደራጀትና በመለየት በተከሳሹ ላይ ክስ መስርቷል።
የቀረበው ክስም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 15 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፏል የሚል ነው።
ተከሳሹ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በሀብት ምርመራና ማስተዳደር ዋና ክፍል ስር የአደገኛ ዕጽ ኤግዚቢት አስተዳደር የስራ መደብ ተመድቦ በመስራት ላይ እያለ÷ በ2015 ዓ.ም በተለያዩ ወራት ከተለያዩ ተጠርጣሪዎች የተያዙ የተለያየ መጠን ያላቸው የኮኬይን አደገኛ ዕጾችን በኤግዚቢትነት ከተረከበ በኋላ ዕፆቹን በመሰወርና በሌላ ንጥረ ነገር ተቀይረው መገኘታቸውን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበታል።
በዚህም ተከሳሹ በ2015 ዓ.ም በተለያዩ ወራት ከተለያዩ ግለሰቦች የተለያየ መጠን ያላቸው የተያዙ ኮኬይን ዕፆችን ተረክቦ ዕጹን ለማስወገድ ሲፈተሸ የጠፋ መሆኑ በክሱ ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ ተከሳሹ በስራ ላይ በአደራ የተረከበውን ከተለያዩ ተጠርጣሪዎች እጅ የተያዘን 16 ነጥብ 2 ኪሎ ግራም የኮኬይን ዕጽ ያጠፋና አይነቱን በሌላ ኮኬይን ባልሆነ ንጥረ ነገር የቀየረ በመሆኑ በፈጸመው በስራ ተግባር የሚፈጸም የመውሰድና የመሰወር የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።
ዐቃቤ ሕግ ካቀረበው የክስ ዝርዝር ጋር የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አያይዞ አቅርቧል።
ተከሳሹ በተረኛ ችሎት ቀርቦ ክሱ ከደረሰውና ከተነበበለት በኋላ የዋስትና ጥያቄ ቢያቀርብም÷ ዐቃቤ ህግ ዋስትና ጥያቄውን በመቃወም ተከራክሯል፡፡
ፍርድ ቤቱም መርምሮ ከቀረበው ክስ አንጻር ዋስትና ሊሰጥ አይገባም በማለት ጥያቄውን ውድቅ አድርጓል።
ተከሳሹ የክስ መቃወሚያ ካለው ለመጠባበቅ ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም ተቀጥሯል።
በታሪክ አዱኛ

