አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢሬቻ የአዲስ አበባ ከተማን የቱሪስት መዳረሻነትና ገቢ በማሳደግ ረገድ ትልቅ አስተዋኦ አለው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡
ከንቲባዋ 5ኛው የኢሬቻ ፎረም መከናወንን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ተፈጥሮን ውብ አድርጎ የፈጠረውን ፈጣሪ የሚያመሰግንበትና የሚያከብርበት፣ የተጣላ ጸቡን በይቅርታ የሚሽርበት፣ የሰላም፣ የአብሮነትና የአንድነት መገለጫ ነው ብለዋል።
ነዋሪዎች በአምስቱም በሮች የሚገቡ እንግዶችን በፍቅር እየተቀበሉ ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በተግባር በማሳየት አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ተምሳሌት መሆኗን ማስመስከራቸውን ገልጸዋል።
ኢሬቻ የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻነትና ገቢ በማሳደግ ረገድ ትልቅ አስተዋኦ አለው ያሉት ከንቲባዋ፤ የከተማ አስተዳደሩም በዓሉን ለመታደም የመጡ በርካታ የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን በክብር እያስተናገደ ይገኛል ብለዋል።
ህዝቡ የኢሬቻ ዕሴት ያልሆኑና መታየት የማይገባቸውን ድርጊቶች ከመፈጸም በመቆጠብ በዓሉን በፍቅር፣ በአንድነትና በድምቀት እንዲያከብርም ጥሪ ማስተላለፋቸውን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።
ለመርሐ ግብሩ መሳካት አስተዋፅዖ ላደረጉ አባገዳዎች፣ ሀደ ስንቄዎች፣ ፎሌዎች፣ አመራሮች፣ የጸጥታ አካላት፣ የሰላም ሠራዊት አባላትና መላው የከተማዋ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!