አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ከኦሮሞ ወንድም እና እህት ህዝቦች ጋር የሚጋራቸው መልካም እሴቶች በርካታ ናቸው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የኢሬቻ በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ጭጋጋማው የክረምት ወራት በብርሃን ጸዳል ሲፈካ በሰላም ላሸጋገረው አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል ነው ብለዋል።
ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመሆን በአደባባይ በደስታ፣ በፍቅርና በአብሮነት የሚያከብረው ድንቅ የባህል እሴቶቻችን መገለጫ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተውጣጡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና ሌሎች እንግዶች ይህንን ውብ በዓል ለማክበር በመታደም ላይ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።
የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተራራቀ የሚቀራረብበት፣ የፍቅር የመቻቻል እና የምስጋና በዓል የሆነው የኢሬቻ በዓል ሲከበር ልዩ የደስታ ስሜት የሚፈጥር መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ በመመልዕክታቸው አንስተዋል።
የክልሉ ህዝብ በተፈጥሯዊ የመሬት አቀማመጥ እና በድንበር ሳይገደብ ከኦሮሞ ወንድም እና እህት ህዝቦች ጋር የሚጋራቸው መልካም እሴቶች በርካታ ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የሁለቱን ክልል ህዝቦች ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለንም ብለዋል።
በመጨረሻም በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የአብሮነት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን መግለፃቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!