Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አቶ ሙስጠፌ ሙሀሙድ ለኢሬቻ በአል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 25 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀሙድ ለመላው ወንድም የኦሮሞ ሕዝብ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ለኢሬቻ በአል በሰላም አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።

በወንድም የኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ዘመናትን በተሻገረ ባህል መሠረት ለምለም ቄጠማ በመያዝ የሚከበረው የኢሬቻ በአል ከጨለማው የክረምት ወራት ብሩህ ወደ ሆነው የመፀው ጊዜ ላሸጋገረ ፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት ታላቅ በአል ነው ብለዋል።

በልምላሜና በብሩህ ተስፋ ደምቆ የሚከበረው የኢሬቻ በአል በክረምቱ ወራት ተራርቆ የከረመው ሕዝብ ዳግም ተገናኝቶና ተሰባስቦ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበትና አብሮነቱን የሚያጠናክርበት የአንድነት በአል መሆኑንም ገልጸዋል።

የተጣላና የተቀያየመ ተቀራርቦ በመነጋገር ሰላምና እርቅ ሳያወርድ በበአሉ ላይ መገኘትን የሚከለክለው የኢሬቻ በአል ያለፈ ቂምና ጥላቻ በፍቅር የሚታከምበት የይቅርታ በአል ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በአጠቃላይ የኢሬቻ በአል የኦሮሞ ሕዝብ መልካም እሴቶች ጎልተውና ደምቀው የሚገለጡበት ታላቅ በአል በመሆኑ የሶማሌ ክልላዊ መንግስት እነዚህ ድንቅ እሴቶች በክልሉ ሕዝብ ዘንድ ታውቀው የሁላችንም የጋራ እሴት እንዲሆኑ አበክሮ የሚሰራ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁም ብለዋል በመልዕክታቸው።

በመጨረሻም የዘንድሮው የኢሬቻ በአል እንደ ሁልጊዜው የኦሮሞ ሕዝብ ባሕል ፣ ወግና መልካም እሴቶች ሁሉ በውበትና በድምቀት ጎልተው የሚታዩበት የሰላም ፣ የፍቅርና የደስታ በአል እንዲሆን መልካም ምኞቴን እየገለፅኩ በድጋሚ እንኳን አደረሳችሁ እንኳን አደረሰን እላለሁ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

Exit mobile version