Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለ26 ዓመታት ሽሽት ላይ የነበረ የሩዋንዳ ዘር ፍጅት ወንጀል ተጠርጠጣሪ ፈረንሳይ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለ26 ዓመታት ሽሽት ላይ የነበረ የሩዋንዳ ዘር ፍጅት ወንጀል ተጠርጠጣሪ ፍሊሸን ካጉባ ፈረንሳይ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለፀ።

ለሚሊሽያዎች ገንዘብ በመስጠት 800 ሺህ ያክል ሰዎች እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል በሚል ወንጀል የተጠረጠረው ግለሰቡ በዛሬው እለት ፓሪስ አቅራቢያ በቁጥጥር ስር መዋሉን የፈረንሳይ የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የ84 ዓመቱ ሩዋንዳዊ ፍሊሸን ካጉባ ሀሰተኛ ማንነት በመጠቀም ሲኖር እንደነበረም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

ፍሊሸን ካጉባ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1997 በሩዋንዳ በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ውስጥ በተለይም በ1994 ላይ የተፈፀመው የዘር ፍጅትን ጨምሮ በሰባት ወንጀሎች ከተከሰሰ በኋላ በሽሽት ላይ ነው የቆየው።

በሩዋንዳ ሁቱ እና ቱትሲ ጎሳዎች መካከል በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1990ዎቹ ውስጥ ከፍተኛ የእርስ በእስር ጦርነት መካሄዱ ይታወሳል።

ሩዋንዳዊው ባለሀብት ፍሊሸን ካጉባም ለሚሊሻዎች ድጋፍ በማድረግ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1994 ለ100 ቀናት በተካሄደው የዘር ጭፍጨፋ ላይ 800 ሺህ ያክል የቱትሲ ጉሳዎች እና የዘር ፍጅቱን የማይቀበሉ ሁቱዎች እንዲሞቱ አድርጓል በሚል መጠርጠሩ ተነግሯል።

በአውሮፓውያኑ ከ1994 ጀምሮም ፍሊሸን ካጉባ የተለያዩ የሀሰት ማምነቶችን በመጠቀም በጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ኮንጎ ኪንሻሳ፣ ኬንያ እና ሲወዘርላንድ ውስጥ ሲኖር እንደነበረም ዛሬ በወጣው መግለጫ ተመላክቷል።

በቁጥጥር ስር የዋለው የወንጀል ተጠርጣሪም መጀመሪያ በፈረንሳይ ፍርድ ቤት ቀጥሎም ሄግ በሚገኘው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብም ተነግሯል።

አውግስቲን ቢዚማና እና ፓሮቲስ ማፕሪያና የተባሉ ሁለት በዘር ማጥፋት ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች አሁንም በዓለም አቀፉ የህትፍ አካላት ክትትል እና ፍለጋ እየተደረገባቸው መሆኑም ታውቋል።

ሩዋንዳዊው ባለሀብት ፍሊሸን ካጉባ በቁጥጥር ስር መዋልም ምንም እንኳ ወንጀሉ ከተሰራ ከ26 ዓመታት በላይ ቢሆንም በዘር ፍጅት ወንጀል የተካፈለ ማንኛውም ግለሰብ ለፍርድ እንደሚቀርብ ማሳያ ነው ተብሏል።

ምንጭ፦ reuters.com

Exit mobile version